ሀዋሳ፡ ሕዳር 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኢትዮጵያዊያን የመረዳዳትና መከባበር ባህል መዳበር ውስጥ የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
በ2016 ዓ.ም በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተመዘገበው ስኬት የበኩላቸውን ላበረከቱ የመንግስትና የግል ተቋማት የዕውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር በዞኑ ዲላ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በመርሀ ግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ፤ የጌዴኦ ዞን በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባስመዘገበው ስኬት በክልል ደረጃ ዕውቅና በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በተለይም የአቅመ ደካማ እናቶችና አጋዥ የሌላቸውን አረጋዊያንን እንባ ለማበስ በቤት ግንባታው ዘርፍ ዞኑ እያከናወነ የሚገኘው ተግባር በክልሉ ለሚገኙ ዞኖችም ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልደ(ዶ/ር) የክረምት ወራት በጎ አገልግሎት በኢትየጵያዊያን የመረዳዳትና መከባበር ባህል መዳበር ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸው 3 ሺህ 5 መቶ 18 የአቅመ ደካሞችን ቤት በመገንባትና በማደስ ከነበሩበት አስቸጋሪ ህይወት እንዲወጡ ከመርዳት አኳያ ዞኑ መልካም ተግባር መፈፀሙን አስታውቀዋል፡፡
ከእነዚህ ቤቶች 1 ሺህ 8 መቶ 96 ቤቶች በአንድ ጀንበር ተገንብተው የተላለፉ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ዝናቡ ለዚህ ስኬት ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና ሌሎች መዋቅሮች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከወጣቶቹ ጎን በመሆን ለሰሩት በጎ ሥራ አመስግነዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደግነት ኃይሉ፤ በዞኑ ተለይተው ወደ ተግባር በተገቡ 15 የሚሆኑ የአገልግሎት ዘርፎች በተከናወነው ሥራ መንግስት ያወጣ የነበረውን ከ5 መቶ 53 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ገልፀው፤ በዚህ ሥራ ለተሳተፉ ወጣቶችና ለተግባሩ ስኬታማነት በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን ላበረከቱ ተቋማት ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡
በመጨረሻም በ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ መዋቅሮችና ባለድርሻ አካላት የዕውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር በማካሄድ መድረኩ ተጠናቀዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ