ሊቨርፑልና ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ ታላቅ ጨዋታን ዛሬ ምሽት ያካሂዳሉ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 5ኛ ዙር ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት 9 ጨዋታዎች ሲካሄዱ በአንፊልድ ሮድ ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ ጋር የሚያከናውኑት ጨዋታ ከወዲሁ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ሻምፒዮንስ ሊጉ በአዲስ አቀራረብ መካሄድ በጀመረበት በያዝነው ዓመት ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ብቸኛው ክለብ የሆነው ሊቨርፑል ወጥ ብቃቱን ለማስቀጠል ከወቅቱ የሻምፒዮንስ ሊጉ ባለክብር ከሆነው ሪያል ማድሪድ ጋር ይፋጠጣል።
ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ካከናወናቸው 4 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች መካከል 2 ሲያሸንፍ በ2 ጨዋታዎች ተረቷል።
ሎስብላንኮው በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታው በኤሲ ሚላን 3ለ1 መረታቱ አይዘነጋም።
በሊቨርፑል በኩል አሌክሳንደር አርኖልድ ወደ ልምምድ መመለሱ ሲገለፅ በሪያል ማድሪድ በኩል ግን ቨኒሺዬስ ጁኒዬር በጉዳት ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ምሽት 2 ሠዓት ከ45 ላይ ሁለት መርሐግብሮች ሲካሄዱ የሰርቢያው ሬድ ስታር ቤልግሬድ ከጀርመኑ ስቱትጋርት እንዲሁም የኦትስሪያው ስትሩም ግራዝ ከስፔኑ ጂሮና ይጫወታሉ፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሠዓት ላይ ደግሞ አስቶንቪላ ከጁቬንቱስ፣ቦሎኛ ከሊል፣ ሴልቲክ ከክለብ ብሩጅ፣ ዳይናሞ ዛግሬብ ከቡሩሺያ ዶርቱመንድ፣ሞናኮ ከቤኒፊካ እንዲሁም ፒኤስቪ ከሻካታር ዶኔስክ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ፡፡
አርሰናል፣ ባርሴሎና እና ባየርን ሙኒክ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ጥሏል፡፡
ትናንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ስፖርቲንግ የገጠመው አርሰናል 5ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።
በአሊያንዝ አሬና ፒኤስጂን ያስተናገደው ባየርን ሙኒክ ኪም ምንጃኤ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1ለ0 ረቷል።
ባርሴሎናም በሜዳው የፈረንሳዩን ክለብ ብረስትን አስተናግዶ 3ለ0 አሸንፏል።
በኤቲሐድ ስታዲየም ማንቸስተር ሲቲ ከሆላንዱ ክለብ ፌዬኖርድ ጋር ባከናወነው ጨዋታ 3ለ0 ሲመራ ቆይታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች አቻ ሆኖ ነጥብ ጥሏል።
በሌሎች ጨዋታዎች ባየርሊቨርኩሰን ሳልዝበርግን 5ለ0፣ ኢንተር ሚላን ሌይፕዚችን 1ለ0 እንዲሁም አታላንታ ከሜዳው ውጪ ያንግቦይስን 6ለ1 በሆነ ውጤት መርታት ችሏል።
በሙሉቀን ባሳ
More Stories
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 6ኛ ዙር መርሐግብር 9 ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ
ሩድ ቫኔስትሮይ የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሆኖ በይፋ ተሾመ
የሁለቱ ወንድማማቾች ወግ