አርሰናል ሊድስን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመለሰ
በ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መሪው አርሰናል ወደ ዮርክሻይር አምርቶ ሊድስ ዩናይትድ 4 ለ ዐ በመርታት ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
በኢላንድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የመድፈኞቹን የማሸነፊያ ግቦች ማርቲን ዙብሜንዲ ፣ ካርል ዳርሎው በራሱ ላይ ፣ ቪክቶር ዮኬሬሽ እና ጋብርኤል ጄሱስ አስገኝተዋል።
ስፔናዊው አማካይ ማርቲን ዙብሜንዲ በፕሪሚዬር ሊጉ አራተኛ ጎሉን ለአርሰናል አስቆጥሯል።
ከ11 የሊግ ጨዋታዎች በኋላ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ጎል ማስቆጠር የቻለው ግዮኬሬሽ ደግሞ በፕሪሚዬር ሊጉ ያስቆጠራቸውን ጎሎች 6 አድርሷል።
በጨዋታው ላይ በሁለቱም ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ የቻለው ኖኒ ማዱዌኬ በአርሰናል ቤት የመጀመሪያ የፕሪሚዬር ሊግ አሲስቱን አስመዝግቧል።
ካይ ሀቨርትዝ ከ363 ቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምዬርሊጉ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ጨዋታ ጀምሯል።
አርሰናል በኢላንድ ሮድ ጨዋታን ከተሸነፈ 26 ዓመታት አልፈውታል።
አርሰናል ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 53 በማድረስ ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ በሰባት ነጥብ በልጦ መሪነቱን አጠናክሯል።
10ኛ የሊግ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሊድስ በአንፃሩ በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሌሎች ጨዋታዎች ብራይተን በሜዳው ከኤቨርተን 1 ለ 1 ሲለያይ ቦርማውዝ በበኩሉ ከሜዳው ውጪ ዎልቭስን 2 ለ 0 ረቷል።
ፕሪሚዬርሊጉ መካሄዱን ሲቀጥል ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በለንደን ደርቢ ቼልሲ እና ዌስትሃም በስታምፎርድ ብሪጅ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
እንዲሁም ምሽት 5 ሰዓት ላይ የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን በሜዳው ኒውካስልን ያስተናግዳሉ።
በአንፊልድ በሚካሄደው ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ከሽንፈት ለማገገም ይፋጠጣሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት ሊቨርፑል በቦርንማውዝ ኒውካስል በበኩሉ በአስቶንቫላ መሸነፋቸው ይታወሳል።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና የሴቶች ሩጫ በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ ተካሄደ
ማክስ ዳውማን ከአርሰናል ጋር የስኮላርሺፕ ውል ተፈራረመ
ፓትሪክ ዶርጉ ለ10 ሳምንታት ያኽል ከሜዳ ሊርቅ ነው