የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት አጋር ተቋማት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናገሩ
ተቋማቱ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ጋር በቦንጋ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን ተ.መ.ድ ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ እንዲደግፍ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ የስራ ሁኔታዎችና ከባቢዎች ያሏት ሀገር በመሆኗ በትብብር መስራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በተለይም በወባ በሽታ መከላከል ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ለማገዝ ዕቅድ መያዙንም አሳውቀዋል።
በተ.መ.ድ ስር የሚሰሩ ሁሉም አጋር ድርጅቶች ስራዎቻቸውን በመናበብ እንዲያከናውኑ ማድረግ ከተቻለ የክልሉንና የኢትዮጵያን ሁሉ አቀፍ ስራዎች ማሣካት እንደሚቻል አመላክተዋል።
የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ኦርላንዶ ሶሳ የአርሶ አደሮችን ገቢ እና ዘርፉን ለማሣደግ የሚሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በአሳ እና በሩዝ ምርት ላይ በክልሉ የሚሰሩ ስራዎችን ተቋሙ እንደሚደግፍ አሳውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ሙቲንታ ሃምባይ በበኩላቸው፤ በምግብ ዋስትና መረጋገጥና በትምህርት ቤት ምገባ ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶችን በበጀትና በስልጠና በመደገፍ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ክልሉን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አሰግድ አዳነ፤ የኢንዱስትሪ እድገትን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁሉም ዘርፍ መንግስት የያዛቸውን ከጥገኝነት የመላቀቅ እቅዶች በመደገፍ የገጠር ሽግግርን በማጠናከርና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ድጋፍ በማድረግ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በማመላከት፤ ይህንን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
ድርጅቱ የስራ እድልን በመፍጠርና በምርቶች ላይ እሴት በመጨመር እንዲሸጡ በማስቻል የአምራቹን ገቢ ለማሣደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ሁሉም የተ.መ.ድ ተቋማት በክልሉ የሚሰሩ ስራዎች እንዲሳኩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ተግባራትን አከናውነዋል ብለዋል።
የእናቶችን እና ህፃናትን ሞት፣ ውሃ-ወለድ በሽታዎችን እና ሌሎችንም የጤና ችግሮችን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ በተለይም በእነዚህ ዘርፎች የተቋማቱ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በርካታ አጋሮችን እና ግብረ-ሠናይ ድርጅቶችን በማስተባበር በሁሉም ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሺህ 273 መዝገቦች በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ማግኘታቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ
የተፈጠረላቸውን የሥራ ዕድል ተጠቅመው በመሥራታቸው የተሻለ ለውጥ እያገኙ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ተወያይቶ አፀደቀ