የሁለቱ ወንድማማቾች ወግ
በአስፋው አማረ
እያንዳንዱ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ወደ ስኬት በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ የራሱ የትግል ታሪክ አለው። ይህ የፅናታቸው እና የስኬት መንገዳቸውን ለመጥረግ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
በዛሬው ዳሰሳችንም እያበበ ስለመጣው ስፔናዊው የኳስ ጥበበኛ ኒኮ ዊሊያምስ እና ታላቅ ወንድሙ ኢኛኪ ዊሊያምስ አነቃቂ የህይወት ታሪክ ልናጋራችሁ ወደድን። እነሆ!
ሙሉ ስሙ ኒኮላስ ዊሊያምስ አርተር ይባላል፡፡ የተወለደው እ.ኤ.አ ሐምሌ 12 ቀን 2002 ነው፡፡ ወላጆቹ ማሪያ አርተር (እናቱ) እና ፊሊክስ ዊሊያምስ (አባቱ) በታሪካዊቷ ፓምሎና ስፔን ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት ነው የተወለደው።
ኒኮ ዊሊያምስ ታላቅ ወንድም ሲኖረው ኢኛኪ ዊሊያምስ ይባላል፡፡ ወንድማማቾቹ በጣም የሚዋደዱ ናቸው፡፡ የኒኮ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እጅግ በጣም ከባድ ነበሩ፡፡ ወጣቱ ኒኮ ቤተሰቡን ከድህነት የማውጣት ህልም ነበረው።
የኒኮ ዊሊያምስ ወላጆች ሁልጊዜ ኑሮአቸውን ለማሟላት ሲሉ ያለማቋረጥ ይሠሩ ነበር። ወጣቱ ኒኮ ያደገው በታላቅ ወንድሙ እንክብካቤ ነበር። ሁለቱም ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ ነበር፡፡
ወንድማማቾቹ በልጅነታቸው ለሚያልሙት ክለቦች የመጫወት ህልም ነበራቸው። ኒኮ ከልጅነቱ ጀምሮ የአትሌቲክ ቢልባኦ ቀንደኛ ደጋፊ ሲሆን ለታታሪነቱ እና ቆራጥነቱ ምስክርነቱ አሁን ለስፔን ቡድን መጫወቱ ነው።
የኒኮ ዊሊያምስ እናት ማሪያ አርቱር ለልጆቿ የተረጋጋ ህይወት ለመስጠት እና ኑሯቸውን ለማሟላት ብቻ እጅግ በጣም ጠንክራ ሠርታለች። እሷ እና ባለቤቷ ጋናን የለቀቁት ለልጆቿ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የኒኮን ታላቅ ወንድም በፀነሰች ጊዜ ነበር።
ጥንዶቹ ረሃብን፣ ጥማትን፣ እና ሌሎች በርካታ አደጋዎችን ሲታገሉ በባዶ እግራቸው በሰሃራ በረሃ አልፈዋል። ከዚያም ወደ ስፔን ለመድረስ የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው በመጨረሻ የድንበሩን አጥር ለማለፍ ሲሞክሩ ተያዙ።
ማሪያ አንድ የካቶሊክ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጠበቃ ከእስር እንዳዳናቸው ታስታውሳለች፡፡ ጠበቃው ከጋና ወደ ስፔን በተደረገው ጉዞ በአደጋው እና በአስከፊው ሁኔታ መጸጸቱን አምኗል። ጥንዶቹ የመጀመሪያ ልጃቸውን ባዳነላቸው ቄስ ስም ጠሩት።
ማሪያ አርቱር የወንድ ልጆቿን ግጥሚያዎች ለመመልከት ሁልጊዜ በስቴዲየሞች ትገኛለች። የአትሌቲክስ ስፖርት ዳይሬክተር ማይክል ጎንዛሌዝ እንዳሉት እናታቸው ለመሻሻላቸው ቁልፍ ሚና ነበራት፡፡
ፊሊክስ ዊሊያምስ የኒኮ ዊሊያምስ አባት ነው። ልጆቹ የተረጋጋ የልጅነት ጊዜ እንዲሰጣቸው ለማድረግ ጠንክሮ ሰርቷል። ወላጆቻቸው ትግላቸው እና ጽናታቸው ልጆቻቸው ዛሬ ላይ ያገኙት ስኬት አካል እንዲለብስ በመልካም ስነ ምግባር ቀርጸዋቸዋል።
ከኒኮ ዊሊያምስ ጋር አብሮ ያደገው ኢኛኪ ዊሊያምስ በትርፍ ሰዓቱ ወላጆቻቸው በማይኖሩበት ጊዜ ወንድሙን በመንከባከብ ነበር የሚያሳልፈው። ኢኛኪ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን በመዳኘትም ለቤተሰቡ ገቢ ያስገኝ ነበር። ኢኛኪ ዊሊያምስ የስፔኑን ክለብ አትሌቲክ ቢልባኦን አካዳሚ የተቀላቀለው በ18 ዓመቱ ሲሆን ይህም ወንድሙ የእሱን ፈለግ እንዲከተል አድርጓል። ኒኮ እና ታላቅ ወንድሙ ኢኛኪ የልጅነት ጊዜያቸውን በሙሉ አብረው እየተጫወቱ ነበር ያሳለፉት። ኒኮ በ12 አመቱ የቢልባኦን አካዳሚ ተቀላቅሏል፤ ነገር ግን ታላቅ ወንድሙ ኢኛኪ ቀድሞውንም ወደ ዋናው ቡድን ተቀላቅሎ ነበር።
ኒኮ ዊሊያምስ ዕድሜው 22 እስኪሞላው ድረስ ለሁለት ክለቦች ተጫውቷል። ህልሙ ወደ ነበረው አትሌቲክ ቢልባኦ ክለብ ከመግባቱ በፊት በሲኤ ኦሳሱና(CA Osasuna) የወጣቶች ቡድን ዝግጅት ማድረግ ነበረበት።
ግን ብዙም ሳይቆይ ኒኮ ይደግፈው የነበረውን ክለብ ቢልባኦን በ12 አመቱ ተቀላቀለ፡፡ የወደፊት ህይወቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወሰነ።
በክለቡ ውስጥ ቀናቶች እየተቆጠሩ ሲሄዱ ኒኮ በሜዳ ውስጥ በሚያሳየው አስደናቂ የእግር ኳስ ትርኢቶች በየጊዜው መሻሻል አሳይቷል። የቢልባኦ የመጀመሪያ ቡድን አሰልጣኞችን በመማረክም ቀስ በቀስ ወደ መጀመሪያው ቡድን አደገ። በዋናው ቡድንም በየካቲት ወር 2015 በዩሮፓ ሊግ ቡድኑ ከጣሊያኑ ቶሪኖ ጋር ሲጫወት ጎል በማስቆጠር ጅማሮውን ማሳመር ችሏል፡፡
በ2016 በእያንዳንዱ የላሊጋ ጨዋታ በግሉ የማይታመን ግስጋሴ አድርጎ ነበር። ስለግል ሕይወቱም ሲናገር፡-
“በጣም ጥሩ ጂኖች አሉኝ፡፡ አያቴ 90 ዓመቱ ነው፡፡ ግን አሁንም ጠዋት ጠዋት በየሜዳው ለሶስት ሰአት በእግር ይጓዛል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ራሴን በደንብ ለመንከባከብ፣ ለመብላት፣ ለማረፍ እና ጸጥ ያለ ህይወት እንዲኖረኝ መሞከር አለብኝ። አሰልጣኙ በሚፈልገኝ ጊዜ ሁሉ እንድገኝ ያግዘኛል።” ይላል፡፡
እስከዛሬ ኒኮ እና ወንድሙ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ አስደናቂ አጋርነት አላቸው። ለሚወዱት ክለብ በመጫወት ለራሳቸው ጥሩ ስም ገንብተዋል፡፡
የኒኮ ዊሊያምስ የእግር ኳስ ሕይወት በተለይም ባለፉት ሁለት ወቅቶች ከፍ ብሏል። ለወጣቱ የቅርብ ጊዜ ስኬቱ በዩሮ 2024 ከስፔን ብሄራዊ ቡድን ጋር ዋንጫውን ከፍ አድርጎ ያነሳበት ነው፡፡
ተጫዋቹ በመድረኩ የፍፃሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን 2ለ1 ስታሸንፍ የመጀመሪያውን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል። በጨዋታው ባሳየው አስደናቂ ብቃት የ”ኮኮብ ተጫዋች” ሽልማት ተበርክቶለታል። በዚሁ የአውሮፓ ዋንጫ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር እያንጸባረቀ ከሚገኘው ወጣቱ ላሚን ያማል ጋር በመጣመር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡
ላሚን ያማል ከባርሴሎና ጋር በውል ተቆራኝቷል፡፡ ኒኮ ዊልያምስም ከያማል ጋር ልክ እንደ ብሄራዊ ቡድኑ በባርሴሎናም አብረው እንዲቆራኙ የብዙ የባርሴሎና ደጋፊዎች ምኞት ነው፡፡ አሁን አስጊው ጉዳይ ከአትሌቲክ ክለብ ጋር ባለው የ3 አመት ኮንትራት 63.2 ሚሊየን ዶላር የውል ማፍረሻ መክፈል ከባርሴሎና መጠበቁ ነው፡፡
ነገር ግን የባርሴሎናው ፕሬዝዳንት ጆአን ላፖርታ የስፔናዊው ባለተሰጥኦ አድናቂ በመሆናቸው በባርሴሎና ለማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ኒኮ ዊሊያምስ በአሁኑ ጊዜ በሳምንት 200 ሺህ ዩውሮ ደመወዝ ተከፋይ ነው በክለቡ አትሌቲክ ቢልባኦ፡፡ ይህም እስከ 10 ሚሊየን 420 ሺህ ዩውሮ በዓመት ከጉርሻ ውጭ ተከፋይ እንዲሆን አድርጎታል። በክለቡም የ3 ዓመታት ውሉ እስኪጠናቀቅ እስከ 2027 ድረስ ተጨማሪ ቆይታ ይኖረዋል።
More Stories
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 6ኛ ዙር መርሐግብር 9 ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ