በጎፋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሺህ 273 መዝገቦች በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ማግኘታቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ

በጎፋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሺህ 273 መዝገቦች በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ማግኘታቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ

መምሪያው የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምና በቀጣይ የትኩረት መስኮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ብላቴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በዞኑ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማክበርና መብትና ጊዴታውን የሚያውቅ ህብረተሰብ ለመፍጠር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሺህ 336 የፍትሐብሄርና ልዩ ልዩ የወንጀል ጉዳዮች የምርመራ መዝገቦች ቀርበው 2 ሺህ 273 መዝገቦች በዐቃቤ ህግ የተለያየ ህጋዊ አስተያየትና ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን የማጥራት ምጣኔ 95 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

መምሪያው የሙስና ወንጀሎችና በታክስና ኢኮኖሚ ወንጀሎች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ህጋዊ ውሳኔ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በዚህም ሊመዘበር የነበረ ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ስለመቻሉ አብራርተዋል።

የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግ ከፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ተቋም ጋር በቅንጅት በመስራት የተሻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

የዞኑ ምክር ቤት ህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለምገነት ላቀው በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ መምሪያው ያከናወናቸው ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን አንስተዋል።

ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እና ህገ ወጥ የመሬት ወረራን መከላከል በቀጣይ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች መሆናቸውን ወ/ሮ ዓለምገነት አብራርተዋል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ፀጋዬ ፅጌ በበኩላቸው፤ ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለማረምና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መክረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀጣይ የተለየ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸምና ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን