የተፈጠረላቸውን የሥራ ዕድል ተጠቅመው በመሥራታቸው የተሻለ ለውጥ እያገኙ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ
የወረዳው ሥራና ክህሎት ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ በ2018 በጀት ዓመት ሥራ አጥ ወጣቶችን ለይቶ በማደራጀት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወደ ተግባር ማስገባቱን ገልጿል።
ወጣት ኤልያስ ከበደ በወረዳው የሐሩ 01 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን በ2018 ዓ.ም በወርሃ ታህሳስ በወረዳው ሥራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ሥር 5 አባላት ሆነው “ዳራሮ” ዘመናዊ የወንዶችና ሴቶች ልብስ ስፌት በሚል ማህበር ተደራጅተው 15 ሺህ ብር በመቆጠብ 1 መቶ 50 ሺህ ብር ከመንግሥት ተበድረው ወደ ሥራ በመግባት በሕይወታቸው በርካታ ለውጦች ማምጣታቸውን አስረድተዋል።
ሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ካፒታላቸውን ወደ 3 መቶ 80 ሺህ ብር በላይ ማድረስ መቻላቸውን የተናገረው ወጣቱ፤ ሥራውን ለማሳደግ የሚረዱ ማሽኞችን ለመግዛት ዕቅድ እንዳላቸው በመጠቆም ላለባቸው የሥራ ቦታን ጥበት ችግር በሚመለከታቸው አካላት እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።
አያይዞም ያለሥራ መቀመጥ ለተለያዩ ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎችና ለድህነት እንደሚያጋልጥ ተናግሮ፤ በአሁኑ ሰዓት የተሻለ ኢኮኖሚ ባለቤቶች መሆናቸውን ተናግሯል።
ሌላኛው በሐሩ ቀበሌ “ሁንጄ ኖጵኖ” የተሰኘው ማህበር ፀሐፊ ወጣት አብርሃም ገላግሌ በበኩሉ፤ በአካባቢያቸው የአቮካዶ ችግኞችን በማፍላትና በማዘጋጀት ሥራ በመሰማራት ለፈላጊ አካላት በማቅረብ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ተናግሯል።
ከዚህም ጎን ለጎን ማህበሩ የቡና ችግኞችን በማፍላት በኢኮኖሚ ራሱን ከመደገፍ አልፎ በግብርናውም ክፍለ ኢኮኖሚ የቡናን ምርትና ምርታማነት ለመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ጠቁሟል።
በይርጋጨፌ ወረዳ ሥራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ጥናትና አደረጃጀት ቡድን መሪ አቶ ዳዊት ጀቦ፤ በወረዳው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ወጣቶች የተመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም በለውጥ ጎዳና ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህም በየደረጃው ካሉ ባለሙያዎች ጋር በቅርበት ሆኖ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በወረዳው በአንድ ቀን ጫጩት፣ ከብት ማደለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በችግኝ አቅርቦትና መሰል በሥራ ዘርፎች ላይ ጥናት በማድረግና በማደራጀት ከ3 ሺህ 5 መቶ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ በቀለ፤ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች በገንዘብ አያያዝ፣ በቢዝነስ ፕላንና አጠቃላይ ማህበራዊ ዕድገት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተው ከኦሞ ባንክ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑትን ዕድል ማመቻቸታውንም ጠቁመዋል።
ወደ ሥራ የገቡ ወጣቶች ከሥራ ቦታ ጥበት ጋር አያይዘው ያነሱት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሠራ መሆኑንም በማከል።
በተለያዩ ጊዜያት ተወስደው ያልተመለሱ ውዝፍ ብድሮችን የማስመለስ ተግባርን በትኩረት በማከናወን ተጨማሪ ብድር ለማመቻቸት በትኩረት ይሠራልም ብለዋል ኃላፊው።
በገንዘብ አቅርቦት በኩሉ ያለባቸውን ችግር ኦሞ ባንክ እንዲፈታ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሺህ 273 መዝገቦች በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ማግኘታቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት አጋር ተቋማት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናገሩ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ተወያይቶ አፀደቀ