“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ ተከበረ

“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ ተከበረ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ ተከብሯል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቤኔዘር ተረፈ በበዓሉ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከድህነት ወደ ብልጽግና እያሸጋገረ ያለና አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የከፈተ ፓርቲ ነው።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በፓርቲው መሪነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተመዘገቡ አመርቂ ስኬቶችና ውጤቶች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

የክልሉ ሕዝቦች የዘመናት ጥያቄ የነበረው የአደረጃጀት ጥያቄ ከሕዝቡ ጋር በብስለት ምክክር በማድረግ በሕዝቦች መፈቃቀድና ውሳኔ የተመለሰበት መንገድ ብልጽግና ፓርቲን ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ እንዲሁም በዲፕሎማሲ ስራዎች ያስመዘገበቻቸው አንጸባራቂ ውጤቶች ፓርቲው በሰጠው በሳል አመራር በመሆኑ የተገኙ ድሎችን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ያሉት የጎፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደለ ያዕቆብ ናቸው።

በመድረኩ “የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ የአምስት ዓመታት ጉዞ የሚያወሳ የመወያያ ሰነድ በክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ መንግስቱ ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ፓርቲው በሁሉም ዘርፎች የጀመሯቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን በመወጣት የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በመድረኩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የሣውላ ክላስተር እና የጎፋ ዞን አመራሮችና ሠራተኞች፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን