የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህዝቦች አንድነትና ልማት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህዝቦች አንድነትና ልማት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህዝቦች አንድነትና ልማት መሳካት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር የህዝቦች አንድነት ተረጋግጦ ለሰፊው ልማት መሳካት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት በደቡብ ኦሞ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ ገለፀ።

19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በደቡብ ኦሞ ዞን ፐብሊክ ሰርቢስ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም በሐመር ወረዳ ማጠቃለያ መርሐ ግብር በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ ቀን ሲሉ የሐመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሣሙኤል ጋርሾ ገልፀዋል።

የመላው ኢትዮጵያዊያን ባህል፣ ትውፊት፣ ወግና እሴቱ እንዲታወቅ ቀኑ ቁልፍ ድርሻ አለው ሲሉ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሐመር ወረዳ የበዓሉ ማጠቃለያ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ አት ሎስንደ ሎኛሱዋ ናቸው።

ህዳር 29/1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ፀድቆ የፌደራል ስርዓቱ ዋስትና ያገኘበት ቀን በመሆኑ ለመላው ህዝብ የአንድነት መገለጫ ሆኖ ይከበራል ያሉት አቶ ሎስንዴ፥ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ ቀን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅ በመሆኑ ትልቅ ደስታ ይሰማናል ብለዋል።

ክልሉ የ19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል አዘጋጅ በመሆኑ ልዩ ኩራት ይሰማናል ያሉት አቶ ሎስንዴ እንግዶችን ለመቀበል እየተጠባበቁ እንደሆነም ገልፀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን 15 ነባር ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖርባት ከመሆኑ ባሻገር ከአራቱም ኢትዮጵያ ማዕዘናት የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ወደ አካባቢው መጥተው ያለ ልዩነት በአንድነት ተፈቃቅረው ኑሮአቸውን የሚመሩበት ትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ዞን ነው ብለዋል።

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም 32 ብሔር ብሔረሰቦችን በአብራኳ አቅፋ በህዝቦች መፈቃቀር ወደ ብልጽግና ከፍታ ለመድረስ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተገናኘ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ “ሃገራዊ መግባባት ለህብረ-ብሄራዊ አንድነት” የበዓሉ መሪ ቃል ሆኖ ተከብሯል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን