ባለፉት 3 ወራት በዞኑ የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸዉ መሆኑ ተገለጸ
ባለፉት 3 ወራት በዞኑ የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸዉ መሆኑን የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በ2017 አንደኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የፓርቲና የመንግስት ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
የአፈፃፀም ሪፖርቱን ያቀረቡት የዞኑ መንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታከለ ታምሩ እንዳሉት፤ ባለፉት 3 ወራት በዞኑ በሁሉም መስኮች የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸዉ ናቸዉ።
በተለይም በግብርና ዘርፍ ላይ በቡና ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ መስኖና መሰል ዘርፎች ላይ የሚታዩ ለዉጦች ቢኖሩም ከፋይዳቸዉ አንጻር ቀጣይ ትኩረት የሚሹ መሆናቸዉን አንስተዋል።
የፓርቲ አደረጃጀቶችን በአግባቡ በማጠናከር ተግባራትን ዉጤታማ ከማድረግ አንጻር በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ተሞክሮችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት መዋቅሮች ጠንካራ ስራ እንደሚጠብቃቸዉም አቶ ታከለ ገልጸዋል።
ዞኑ በተያዘዉ በጀት ዓመት ከ2 ንጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ቢሆንም አሁን ያለዉ አፈጻጸም ወደ 8 መቶ ሚሊዮን አካባቢ በመሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ከማህበራዊ ዘርፍ በጤናን በተመላከተ ወባን መከላከልና በትምህርት ጥራት ላይ እየተሰሩ ያሉ ጅምር እንቅስቃሴዎችን ዉጤታማ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የቀጣይ የመንግስትና የፓርቲ ትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸዉን አመላክተዋል።
መድረኩን የመሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ በበኩላቸዉ፤ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ህብረተሰቡን በማሳተፍ ምላሽ ለመስጠት አመራሩ የተጣለበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም በዞኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየዉን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ባለፈዉ በጀት ዓመት ጠንካራ ተግባር መከናወኑን አንስተዉ፤ አሁን ላይ በየአካባቢዉ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመንገድ ስራዎችን ጨርሶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የዞኑ የኢኮኖሚ አቅም የሆነዉን የቡና ግብይት ህገ-ወጥነት በመከላከል ከዘርፉ የዞኑን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻርም የተቀናጀ ስራ ይጠበቃል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪዉ።
በመድረኩ አስተያየታቸዉን የሰጡት የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ፤ በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ዘርፍ በመኸር አዝመራ የተመረቱ ምርቶችን በማሰባሰቡ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም ታይቷል ብለዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእንሰት ምርት ያለዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አቶ ጋዎ በበልግ አዝመራ የዘር ማስፋት ስራዉ ትኩረት እንደሚደረግበትም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ሕዳር 29 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ በመሆን በባህልና እሴቶቻቸው ደምቀው በአንድነት የሚያከብሩት ልዩ ቀን ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ ተከበረ
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህዝቦች አንድነትና ልማት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ