በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ መብት ወይስ ግዴታ?
በካሱ ብርሃኑ
ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን! እንደምን ከረማችሁ? በዛሬው የህግ-አለ አምዳችን በብዙዎች ዘንድ ሲነገር ስለምንሰማው አንድ ጉዳይ በማንሳት ህጉ-ምን ይላል? የሚለውን ሃሳብ ልናጋራችሁ ወደናል፡፡
መቼም በተለያየ ምክንያት አንድ ሰው በህግ-ጥላ ስር ሲውል “በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አለኝ” ሲል እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ ይህ ሃሳብ ከህግ-አንፃር እንዴት ይታያል? የሚለው የዚህ ሳምንት የህግ-አለ አምዳችን ሊያስቃኛችሁ የመረጠው ርዕሰ-ጉዳይ ነው፡፡
በጽሑፉ አንድ ግለሰብ በወንጀል ተጠርጥሮ ሲያዝ መብቱ ምን ድረስ እንደሆነ የሕግ አንቀፆችን እየጠቀስን ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 10 በተራ ቁጥር ሦስት የተያዙ ሰዎችን መብት በተመለከተ “የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው” ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህ ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡
አያይዞም “ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ እንዲገለጽላቸው መብት አላቸው” ሲልም በግልፅ አሥፍሯል፡፡
በወንጀል ተጠርጥረው ለሚያዙ ሰዎች ሕጉ የመውጣቱ (የመቀመጥ) ዋና እና የመጀመሪያ ዓላማ “መንግሥት በዘፈቀደ እና በመሰለኝ” ሰዎችን በማሰር እንዳያንገላታ እና ስልጣኑን ያለ አግባብ እንዳይጠቀም ገደብ ለማድረግ እንደሆነ በፌደራል የፍትሕ አካላት ማሰልጠኛ ማዕከል የተዘጋጀ ሰነድ እና የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል “ዜጎች ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር ሲውሉ እነዚህ ሕጎች ከተጻፉላቸው አውቀው እና ለይተው መብቶቻቸውን እንዲያስከብሩ ለማድረግ ነው” ሲሉም ያክላሉ፡፡
ሕግ ለሁሉም እኩል ማገልገል እንዳለበት በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በአንቀጽ 25 ሥር ተቀምጧል፡፡ ይህም አንድ ሰው በወንጀል ሲጠረጠር የሚያዝበት ሕግ እና ሥርዓት አለው እንድንል አድርጓል፡፡
ከዚህም ባለፈ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 19 ንኡስ አንቀጽ አንድ ላይ “ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፖሊስ የተከሰሱበትን ሁኔታ በዝርዝር እና በሚገባቸው ቋንቋ በግልጽ ሊነግራቸው እንደሚገባ” በግልፅ አስቀምጧል፡፡
ተጠርጣሪዎች በዚህ ሁኔታ ላይ ፈፀሙት ስለተባለው ወንጀል በሚገባቸው ቋንቋ በግልጽ ሊነገራቸው፣ እነሱም በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቅ፣ የሚሰጡት አስተያየት እንደ ማስረጃ ተቆጥሮ በፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል ሊገለጽላቸው እንደሚገባም ይገልፃል፡፡
ፖሊስ ከተጠርጣሪው ቃል ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩን አጢኖ በዋስ መልቀቅ ይችላል፤ ነገር ግን “በዋስ አይለቀቅም” ካለ በተያዘ በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበትም ይጠቁማል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው፤ ፖሊስ ከተጠርጣሪዎች በማባበያም ሆነ በማስገደድ ቃል መቀበል እንደማይችል ነው፡፡
በማስገደድ እና በኃይል የሚገኝ ማስረጃ በሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት እንደሌለውም በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀፅ 31፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንኡስ ቁጥር አምስት ስር በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት የለውም በሚል ሰፍሯል፡፡ ይሁንና መንግሥት ለተከሳሾች በሚገባቸው ቋንቋ እንዲዳኙ /አገልግሎት እንዲያገኙ/ ገንዘብ ከፍሎ ጠበቃ የማቆም ግዴታ እንዳለበትም ይገልፃል፡፡
ይሁን እንጂ አንድን በወንጀል የተጠረጠረ ዜጋ የፖሊስ አካል ለመያዝ ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በራሱ ደርሶበት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲያስብ፤ ስለግለሰቡ ማንነት ታሳቢ ሊሆኑ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ የተለያዩ የሕግ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ይሄ ማለት ሕጉ ለሁሉም እኩል ተፈጻሚ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ የሚታዩ አካላት ሊኖሩ እንደሚችል የሚያመላክት ነው፡፡
ይህም በሕግ ሥልጣን (ከለላ) የተሰጣቸው የፓርላማ አባላት በሕገ መንግሥቱ ከለላ የተሰጣቸው በመሆኑ በዘፈቀደ “ወንጀል ፈፅማችኋል” ተብለው በፖሊስ ሊያዙ ስለማይችሉ ነው፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 14 ንኡስ አንቀጽ ስድስት ወንጀሉን ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ እስካልተያዙ ድረስ በፖሊስ አይያዙም፣ ሊያዙ የሚችሉት በፓርላማ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በኋላ እንደሆነ በግልፅ አስቀምጧል፡፡
እነዚህን ጨምሮ ማንኛውም በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በሕግ ሥነ ስርዓቱ በተቀመጠው መሰረት ከተያዙ ጀምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ እንደ ንፁህ ሰው የመቆጠር(የመገመት) መብት አላቸው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ማንኛውም በሕግ ጥላ ሥር ያለ ተጠርጣሪ “ክብሩን ከሚያዋርድ ኢሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት የመጠበቅ መብት” እንዳለው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 18 ላይ ኢሰብአዊ አያያዝ ስለመከልከሉ ሰፍሯል። በ1954 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግም በተመሳሳይ እንደሚከለክል መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ይሄም ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች አንዱ ነው፡፡
በሕግ የተያዘ ማንኛውም ሰው በአካሉ እና በክብሩ ላይ ጉዳት ሊደርስበት እንደማይገባ በግልፅ ከመቀመጡም ባለፈ፤ ተጠርጣሪው ሊያመልጥ ሙከራ አድርጓል በሚል ተኩሶ ማቁሰልም ሆነ መደብደብ በሕግ የተከለከለ ስለመሆኑም ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡
በሕገ መንግሥቱ “ፍርድ ቤት ገለልተኛ ነው” ተብሎ ስለሚታሰብ ግራና ቀኙን አይቶ ይወስናል፣ ተከሳሽ የማያምንበት ዳኛ ቢኖር “አላምንበትም ይነሳልኝ” ብሎ እንዲቀየርለት መጠየቅም ይችላል፡፡
በአጠቃላይ በማንኛውም መንገድ ተጠርጣሪዎችን ወንጀለኛ አድርጎ ብዙሃን መገናኛዎችን ጨምሮ ፍርድ ቤት ማስረጃ አይቶ እስካልወሰነ ድረስ የመጨረሻ ጥፋተኛ ናቸው ብሎ መፈረጅ በሕግ የተከለከለ መሆኑንም የተለያዩ ሰነዶች እና የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት እና የተለያዩ የህግ ሰነዶችን ዋቢ አድርገን መጠቀማችንን እየገለፅን የዛሬን በዚሁ አበቃን፡፡ ቸር ይግጠመን ሠላም!
More Stories
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን