የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ግብርን በመክፈል የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን አንዳንድ የገደብ ከተማ ነጋዴዎች ገለጹ

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ግብርን በመክፈል የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን አንዳንድ የገደብ ከተማ ነጋዴዎች ገለጹ

የገደብ ከተማ አስተዳደር ከደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በመጀመሪያው አንድ ቀን 6 ሚሊየን ብር ሰብስቦ ማጠናቀቁን አሰታውቋል።

ግብር ለመክፈል ተገኝተው ካነጋገርናቸው ነጋዴዎች መካከል አቶ አሰፋ ተሰፋዬና ወ/ሮ አስቴር ክፍሌ አሁን ላይ በከተማቸው ያሉ ለውጦች ቀጣይነትን ለመረጋገጥ ግብር በመክፈል የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆነ ጠቁመው፥ የልማት ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም ነጋዴ የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አመላክተዋል።

የገደብ ከተማ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካዬ ፈለቀ ገቢን አሟጦ መሠብሠብ ለልማት ወሳኝ በመሆኑ፥ በገቢ ግብርና በታክስ አስተዳደር አዋጅ መነሻ በትኩረት በመስራታቸው በአንድ ጀንበር 6 ሚሊየን ለመሰብሰብ አቅደው ሙሉ በሙሉ ማሳካታቸውን ተናግረዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከግብ እንዲደርስ ነጋዴዎች የወቅቱን ግብር በወቅቱ መክፈል እንዳለባቸው በመገንዘብ በግንባር ቀደምትነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበው፥ የነጋዴውን ማህበረሰብ የገቢ ስወራና ማጭበርበርን በመከላከል ደረጃዎችን ለማሻሻል እንደሚሠሩ አመላክተዋል።

የገደብ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታሪኩ ሮባ አሁን ለይ ከተማው ላይ እየታዩ ያሉትን ለውጦች ለማስቀጠልና የከተማውን ደረጃ ለማሳደግ በአንደ ጀንበር ከደረጃ “ሐ” ግብር በመሰብሠብ ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።

በተለይም አሁን ላይ በከተማ ያሉ የልማትና የዘመናት ጥያቄ የነበሩትን የመሠረተ ልማት ስራዎች በትኩረት በመተግበሩ የንግድ ማህበረሰቡ ይህን በውል በመገንዝብ በማለዳ የግብር ግዴታውን መወጣት መቻላቸውን ከንቲባ አመላክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጰያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ፈለቀ ግብር የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለው፣ ትላንት የነበረንን ታሪክ በመቀየር ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚገባ እና ገቢን የሚሠውርና የሚያጭበረብር ሳይሆን ደረሰኝ የሚሠጥንና የሚቀበል ማህረሰብን በመፍጠር ልማትን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፋት መልዕክት ማህበረሰባችን ከመንግስት ጎን በመቆም የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ግብር በአግባቡ መክፈል ወሳኝ በመሆኑ የንግዱ ማህረሰብ ላሳየው ተነሳሽነት አመስግነዋል።

በ2017 በደረጃ ሐ ግብር አከፋፈል ሂደት የተለያዩ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራር አካላት፣ የባህል ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን በማለዳ ተነስተው ግዴታቸውን ለተወጡ የንግዱ ማህበረሰብ ነጋዴዎች የማበረታችቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ: ጽጌ ደምሴ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን