የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስፋፋት የእርባታ ስራውን ምርታማነት የማሳደግና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስፋፋት የእርባታ ስራውን ምርታማነት የማሳደግና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

በግቢው እየተከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ የግብርና ስራ ተቋሙን የልህቀት ማዕከል ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቅሷል።

ከአራተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚጠቀሰው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል ትኩረት ያደረጉ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን የእንስሳት ሀብቱ ላይ የተለየ ትኩረት ማድረጉ ተጠቁሟል።

በከፍተኛ የእንሰሳት ሀብቱ በሚጠቀሰው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ ያለውን የእንስሳት ሀብት በሳይንሳዊ ዘዴ በማምረት የአርብቶና አርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኩሴ ጉድሼ የተናገሩት።

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበትና አዲስ የእንስሳት ዝርያ የማሻሻል መርሃ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በግቢው በዶሮ፣ በግና ፍየል፣ የወተት ላምና የስጋ በሬዎችን ማድለብን ጨምሮ የመኖ ማምረት ስራዎች በስፋት እየተሰራ ይገኛል።

ዛሬ የተጀመረው የእንስሳት ማዳቀል ስራም የዚሁ አካል ሆኖ ዩኒቨርሲቲው በእንስሳት እርባታው ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አለሙ አይላቴ በበኩላቸው፤ በግቢው የተጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ውጤታማነት ከግቢው አልፎ ለማህበረሰቡ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የቀድሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይኒቲሶ፣ የእንስሳት ማዳቀል ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚያስተባብሩት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር በሪሁ ገ/ኪዳን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ የውጭ ሃገር ዜጎችም ተገኝተዋል።

የእንስሳት ዝርያ የማሻሻያ መርሃ ግብሩ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚያከናውኑት ሲሆን በአካባቢው ያለውን የእንስሳት ሃብት ውጤታማነትን ለማሳደግ የሚሰራበት እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን