በሩብ ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

በሩብ ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ800 ሚሊየን 894 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ፡፡

መምሪያው የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀምና የገጠር መሬት ገቢ አሰባሰብ ቅድመ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚነወር ሃያቱ በዚህ ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዞኑ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ በተገቢው መሰብሰብ እንዲቻል ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ800 ሚሊዮን 894 ሺህ 222 ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም አመላክተዋል።

ገቢን በአግባቡ አሟጦ በመሰብሰብ ህዝቡ የሚፈልገው የልማት ጥያቄ መመለስ ይገባል ያሉት አቶ ሚነወር፥ ለዚህም ሁሉም አመራር እና ፈጻሚ ባለሙያ ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የመምሪያው የደንበኞች አገልግሎት፣ የታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ሷሊህ ጀማል በበኩላቸው ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ለሁሉም የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም በመድረኩ ከዚህ ቀደም በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ የነበሩ ችግሮችን በጥልቀት በመገምገም ለባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ እንደሚፈጠርም ጠቁሟል።

በመድረኩ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የገቢ ሴክተር ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን መድረኩ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

ዘጋቢ: ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን