የፍትህ አስተዳድር ስርዓቱ ብቃትንና ሥነ-ምግባርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ አሳሰበ
የክልሉ የፍትህ ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል ምርመራ ውጤታማነት እና በቅንጅታዊ ስራዎች ዙሪያ የምክክርና የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሚያ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቤተልሔም ዳንኤል፤ የፍትህና የፖሊስ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበትን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
የወንጀል ድርጊት ጥቆማን ከመቀበል እስከ ፍርድ ተፈፃሚነት ደረጃ ያለውን ሂደት በሚመመለከቱ ስራዎች ውስጥ የፖሊስና የፍትህ ተቋማት ሚና የጎላ እንደሆነ አንስተዋል።
የሁለቱ ተቋማት ስራዎች የጋራ ትብብርን እንደሚጠይቁ አመላክተዋል፡፡
የፍትህ እና የፖሊስ ተቋማት መንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር የሀገሪቱንና የክልሉን ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ከወንጀል የመከላከል፣ የህዝብንና የመንግስትን ሠላምና ደህንነት የመጠበቅና የማረጋገጥ ኃላፊነቶች ተጥሎባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም የፍትህ አስተዳድር ስርዓቱ ብቃትንና ስነ-ምግባርን መሰረት ያደረገ፣ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እስካሁን ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በዐቃቤ ህግና በፖሊስ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ላይ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ እንደሚገኙ ወይዘሮ ቤተልሔም ጠቁመዋል።
የፍትህ አስተዳድር ስርዓቱን ከብልሹ አሰራር የፀዳና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ በአንድ አካል ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ በትብበር መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት የነበረባቸውን ጉዳዮች ነቅሶ በማውጣት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ሁለቱ ተቋማት የሕብረተሰብ ንቃተ-ህግ ሥራን፣ በወንጀል ምርመራ ሂደት የሠብዓዊ መብቶች ጥበቃን፣ በወንጀል ምርመራ ሂደት የምስክሮች እና የጠቋሚዎች ጥበቃን ማሻሻልን እና የመብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ተጠያቂነት ማስፈንን እንዲሁም ሌሎችን ጉዳዮች በሚመለከት በትብብርና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ በአፅንኦት አሳስበዋል።
በመድረኩ የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ የስድስቱም ዞኖች የፍትህና የሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲመለሱ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኧሌ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ገለፀ
መንግስት የደን ጭፍጨፋን በመከላከል የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ እስታውቀ
የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ እንዲያስችል ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ