በክረምቱ ወራት ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ አደጋዎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ
ከአለም ባንክ በተገኘው የ300 ሚሊየን ብር ድጋፍ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን የጎርፍ መቀልበሻ ካናል እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ማዕረጉ ማቲዎስ እንደገለጹት፤ ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ በክልሉ ያሉ የአደጋ ስጋቶችን ማስጠናቱንና በክልሉ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ አደጋዎች ተከስተው ጉዳቶችም እንደነበሩ ጠቁመዋል።
በተጠናው ጥናት በክልሉ በአየር ንብረት ለውጥ በተደጋጋሚ ከሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች አንዱ ጎርፍ ሲሆን የመሬት ናዳ መንሸራተትና የመሬት መሰንጠቅ አደጋዎችም የተከሰቱባቸው ቦታዎች መኖራቸውን አመላክተዋል።
በክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል ያሉ ሲሆን የአደጋ ስጋት መሪ መስሪያ ቤቶች የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራዎችን ታሳቢ ያደረገ እቅድ አቅደው እንዲንቀሳቀሱ መደረጉንም ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት አደጋዎቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የነበሩ የክልሉ ነዋሪዎችም ከፍተኛ የንብረት ውድመት የተከሰተባቸው በመሆኑ ከቀያቸው በመፈናቀል በጊዜያዊ መጠለያዎች መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹን መልሶ የማቋቋሙ ስራ የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ነባር የመረዳዳት ባህል በመጠቀም በጋራ የተሰራ መሆኑን የገለጹት ሀላፊው የተሰራው ስራም ውጤታማ እንደነበር ጠቁመዋል።
በተያዘው ክረምትም ተመሳሳይ ጉዳት በነዋሪዎች ላይ እንዳይደርስ የቅድመ ጥንቃቄ መረጃዎች እንዲደርሳቸው ከማድረግ ጀምሮ የጎርፍ ማፈሰሻዎች እየተገነቡና የተገነቡትም በደለል እንዳይሚሉ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚያወጣቸውን ትንበያዎችን በመከታተል ከፍተኛ ዝናብ በሚከሰትባቸው ወቅቶች ለናዳ ለጎርፍ መጥለቅለቅና ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በጊዜያዊ መጠለያዎች ለማስቀመጥ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
አደጋዎች ሲከሰቱ የሌሎችን ድጋፍ ለመሻት ከመቀመጥ ይልቅ በራስ አቅም ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ዝግጁነትም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መቀጠሉን አቶ ማዕረጉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በክልሉ በስልጤ ዞን ምራቅ ስልጢና ስልጢ ወረደ እንዲሁም በሀድያ ዞን ቦዮ ተፋሰስ በሀላባ ዞን አቶቲ ኡሎ እና በዌራ ዲጆ ስንብጣ፣ በሳንኩራ ወረዳ በምስራቅ ጉራጌና በማረቆ ልዩ ወረዳ በከምባታ ዞን ቃጨቢራ ወረዳ በወንኮ ቀበሌ ላይ ዜጎች የመፈናቀልና የንብረት ውድመት አደጋ ተከስቶ እንደነበረም አስተዉሳዋል።
በክልሉ ለአደጋዎች መጠባበቂያ ፈንድ ማሰባሰቢያ መረሃግብር በአዋጅ ተቋቁሞ ፈንድ የማሰባሰቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሀላፊው አክለዋል።
በዚህም በክልሉ ከ500 ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ መዝራት የተቻለ ሲሆን በድህረ መኸር ወቅት ከ30 ሺ ኩንታል በላይ ምርት ማሰባሰብ መቻሉንም አቶ መዕረጉ አብራርተዋል።
ከ2018 ጀምሮ ከሌላ አካል ድጋፍ ሳይፈለግ በራስ አቅም ሰብአዊ ድጋፍ የማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ሀላፊው አብራርተዋል።
በክልሉ ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችሉ የግብርና ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም አክለው ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ታምሬ አበበ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
“አንድነታችንን በማጎልበት የህዝብ ጥቅም የሚያስቀድም ፖለቲካ ማራመድ ይጠበቅብናል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር መሰረት የሆነው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተገለፀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሠላም፣ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንስ ሁለተኛ ቀን ውሎ መካሄድ ጀምሯል