የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር መሰረት የሆነው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተገለፀ

የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር መሰረት የሆነው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ: ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር መሰረት የሆነው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

“ጠንካራ ክልላዊ አንድነትና አብሮነት ለዘላቂ ሠላምና ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሠላም፤ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መድረክ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ አደም ፋራህ፥ “የሀገራችን ብዝሃነት ውበት ማሳያ የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምስረታ ሂደት በሕዝበ ውሳኔ በህዝቦች ሙሉ ተሳትፎ፣ በሕገ መንግስታዊ መንገድ እና በአመራሩ ብስለትና ጥበብ በጥንቃቄ የተመራ በመሆኑ፥ ክልሉ ከ2 አመት ያልዘለለ ዕድሜ ቢኖረውም እንደ ነባር ክልል ሥራውን እንዲሰራ አስችሎታል ብለዋል።

ክልሉ በታሪክ፣ በባህልና በተፈጥሮ እምቅ ፀጋዎች የታደለ ነው ያሉት አቶ አደም፥ በአጠረ ጊዜ የሰላም፣ የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት የመሆን ትልቅ አቅም አለው ነው ያሉት።

በክልሉ ያለውን ለም መሬት፣ የውሃና ማዕድን ሀብት፣ ብዝሃነቱ እና ታታሪ ህዝብ የልማት ምሰሶዎቹ መሆናቸውን አመላክተው፥ ይህን እምቅ አቅም ለመጠቀም በተደረገው ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በፖለቲካው የክልሉን ተቋማት በማደራጀት ወደ መደበኛ ሥራ እንዲገቡ ከመደረጉም ባሻገር የአመራሩን አንድነት የሚያጠናክሩ ሰፋፊ መድረኮች መካሄዳቸውን አመላክተዋል።

በኢኮኖሚው የግብርና ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም ገቢን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ያሉት አቶ አደም፥ በማህበራዊ ዘርፍ ክልላዊ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ጭምር ለተማሪዎች የመጽሐፍ አቅርቦትን የማሳደግ እና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በስፋት የማቋቋም ሥራ የውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።

ለሕብረብሔራዊ አንድነት መጠናከር መሰረት የሆነው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፣ የደቡብ ኢትዮጵ ክልል በሀገራችን 32 ብ/ብ/ሕዝቦችን በማቀፍ በብዝሃነት ቀዳሚ መሆኑ የተሻለ ተጠቃሚ ያደርገዋል ብለዋል።

ክልሉ ያለውን እምቅ አቅም እንዳይጠቀምና የጋራ ብልጽግና እንዳያረጋገጥ እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የተቋማት አለመጠናከር፣ የልሂቃን ክፍፍልና ያልተገባ እንቅስቃሴ እና በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን የሚያስከትሉ ነጠላ ትርክቶችና እኩይ እንቅስቃሴዎች በተለይም ከማንነት ጋር ከተያያዙ ጉዳዮች የአጭር ጊዜ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ዋነኛዎቹ መሆናቸውን ጠቁመው፥ እንደነዚህ አይነት ክፍተቶች መነሻ በማድረግ በባለድርሻ አካላት መካከል የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለሙ የሠላም፤ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንሶች በየደረጃው እንዲካሄዱ መደረጉ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ