የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አርሶአደሮቹ ያነሱት ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ የማዕከል ችግርን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡
በጮርሶ ወረዳ 13 ቡና አምራች ቀበሌያት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የቀድዳ ጉበታ ቀበሌ ተጠቃሽ ነው፡፡ አርሶአደር ተሰማ ጉሚ እና ታምራት በሮ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ምርጥ ዘር በመትከል እና በማስፋፋት የተከሉት ቡና ደርሶ የተሻለ ምርት እያገኙ እንዳሉ ነው የሚናገሩት።
አርሶአደሮቹ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክር፣ ክትትል እና ድጋፍ ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተው፤ ያገኙትን የቡና ምርት የደረሰውን ብቻ በመልቀም በትኩረት እየሠሩ አንደሚገኙ ገልጸዋል።
የረጎ ቀበሌ አርሶ አደር ደሳለኝ ጀቦ እና ሰንበቶ ጠጌ እሽት ቡና በመልቀም ላይ እያሉ ነበር በቡና ማሳቸው አግኝተን ያነጋገርናቸው። በአሁኑ ጊዜ ቡናቸው ደርሶ ፍሬውን የሚያዩበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፤ በጥራት ለቅመው ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማዘጋጀት ለገበያ ቢያቀርቡም የእሼት ቡና ሽያጭ ማዕከል በአቅራብያቸው ባለመኖሩ እስከ ሁለት ሰዓት በመጓዝ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ጥሩ ዋጋ ሸጠው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሰው መንግስት ለገበያው ችግር መፍትኤ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የቀድዳ ጉበታ እና የረጎ ቀበሌ የግብርና ልማት ጽ/ቤት ባለሙያና እና ኃላፊ አቶ ደስታ አየለ እና አስራት በፈቃዱ፤ በእያንዳንዱ ቀበሌ 2 መቶ 74 እና 5 መቶ 89 ሄክታር መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ የደረሰው የቀላ ቡና ለቅሞ እንዲያዘጋጅ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በጥራት ያዘጋጀውን የቡና ምርት ለገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ እንዳይሆን በቂ የገበያ ማዕከል አለመኖሩ ለአርሶአደሩ ተጠቃሚነት ማነቆ ሆኖ የቆየ ችግር መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ አብርሃም ደመቀ የጮርሶ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ናቸው። ለቡና ምርታማነት እና ጥራት ከአርሶ አደሮች ጋር ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሆነ አመላክተዋል።
አርሶአደሩ በጥራት ያዘጋጀውን ቡና ሸጦ ተጠቃሚ እንዲሆን ከዞን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ባለሀብቶች የኢንቨሰትመንት ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየሠሩ መሆናቸውን ተናገረዋል፡፡
ዘጋቢ: አብዶ አያላ – ከይርጋጨፈ ጣቢያችን
More Stories
እምቅ ሀገራዊ ሀብቶቻችን በተሻጋሪ እሳቢያችን በማልማት እንደ ሀገር የተጀመረውን የዕድገት ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
ተቋማት ትክክለኛ እና ጥራት ያላቸውን መረጃዎችን በማደራጀት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
የ40 ዓመታትን ቂም በቀል የሻረው የጎፋዎች የእርቅ ማዕድ የ”ባራንቼ ዎጋ” ስርዓት