ሀዋሳ፡ ሕዳር 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) እንደ አገር ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ዘመቻ ለመስጠት ታቅዶ ዘመቻ መጀመሩን የጤና ሚኒስትር አስታወቀ።
ቀጣይነት ባለው የጤና አጠባበቅ በሴቶች ላይ የሚያከሰተውን የማህፀን በር ካንሰርን መከላከል እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ዕድሜያቸው ከ9-14 ዓመት ለሚሆኑ ልጃገረዶች ከህዳር 9/2017 ዓ/ም ጀምሮ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች የሚሰጥ ዘመቻ በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ ተጀምሯል።
“አስከፊውን የማህፀን በር ካንሰር በሽታ በክትባት እንከላከል” በሚል መሪ ቃል እንደ ዞን ከ21 ሺህ በላይ ሴቶች በክትባት ዘመቻው ለመድረስ ዝግጅት መደረጉ ተጠቁሟል።
ዜጎች ጤናቸው ተጠብቆ በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ ገልፀዋል።
በዘመቻው ከ9 -14 ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች ከሚደርስባቸው የማህፀን በር ካንሰር ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን የዚሁ አካል የሆነው የክትባት ዘመቻ በኣሪ ዞን ጤና መምሪያ እየተሰጠ መሆኑን የመምሪያው ሀላፊ አቶ ይሁን ጋሎ ተናግረዋል ።
የክትባት ዘመቻው በተለያየ ጊዜ ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት የጤና ሚኒስትር የክትባት ባለሙያ አቶ ጅሬኛ ዊርቱ እንደ ሀገር በዘመቻው 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ፣እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ4 መቶ 46 ሺህ በላይ ለሆኑ ሴቶች ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።
በሽታው በሴቶች ላይ ጫና በማሳደር በገዳይነት ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው የታቀደው የክትባት ሽፋን ሙሉ በሙሉ እንዲሳካ ሁሉም የበኩን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ
የትምህርት ጥራትና ውጤት መሻሻል ዙሪያ የሚተገበሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ
እምቅ ሀገራዊ ሀብቶቻችን በተሻጋሪ እሳቢያችን በማልማት እንደ ሀገር የተጀመረውን የዕድገት ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ