በሰላም ግንባታ እንዲሁም በማህራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ከግብ እንዲደርሱ መረባረብ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ መንቴ ሙንዲኖ ገለፁ

በሰላም ግንባታ እንዲሁም በማህራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ከግብ እንዲደርሱ መረባረብ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ መንቴ ሙንዲኖ ገለፁ

በክልሉ በቀቤና ልዩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ 5ተኛ አመት ምስረታን ምክንያት በማድረግ “የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ማህበረሰብ አቀፍ የማስ ስፖርት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ መነቴ ሙንዲኖ እንደገለፁት የብልጽግና ፖርቲ የሚመራው መንግስት በህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ይሁንታና ቅቡሉነት ያለው ከመሆኑም ባሻገር ህዝቡ በፓርቲው ላይ ትልቅ ተስፋ በማሳደር ከመንግስት ጎን ሆኖ ለሀገሪቱ ልማትና ሰላም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻልና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማረም በተሰማራንበት የስራ መስክ ህዝቡን በቅንነት፣ በፍትሃዊነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባ ምክትል አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል፡፡

የጋራ እሴቶችንና ትርክቶችን በማጠናከር በሰላም ግንባታ እንዲሁም በማህራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ከግብ እንዲደርሱ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸው በሀገሪቱ በፖለቲካው፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ ባለፉት አምስት አመታት በተደረገ ርብርብ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ለዚህም የወጣቶች ሚና የጎላ ነው ያሉት አቶ ሞሳ ወጣቶች ለሀገሪቱና ለአካባቢያቸው ሰላምና ብልፅግና እያደረጉት ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

ብልፅግና ፖርቲ የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት በመዘርጋት አካታችና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባቸው ተቋማትን በመገንባት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ያስታወቁት ደግሞ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አቡበክር ዱላ ናቸው፡፡

ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ከብልፅግና ፖርቲ ምስረታ ጀምሮ የተገኙ ቱርፋቶችና ውጤቶችን ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ በመሆኑ መላው ማህበረሰብ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ያሉት ደግሞ የልዩ ወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጁሃር ጀማል ናቸው ፡፡

ለዚህም የማስ ስፖርት ጤናችንን ከማስጠበቅ በተጨማሪ ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና ሰላም ለማረጋገጥ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ በመስራት አካላዊ ጤንነታቸውን ከመጠበቅ ባሻገር በሀገሪቱ እየተከናወኑ ለሚገኙ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ከመንግስት ጎን በመሆን የሚያደርጉትን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን