የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ

በዞኑ ባለፉት 10 ወራት ብቻ ከ21 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን መምሪያው ጠቁሟል።

በሽታውን ለመከላከል ጉድለቶችን የማረም ስራ እየተሰራ ይገኛልም ተብሏል።

በኮንሶ ዞን በካራት ጤና ጣቢያ ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ ጉይታ ገሌቦ፣ ኩሴ ቶራይቶ እና ወ/ሮ የብቻዬ ሳዋራ፤ በአካባቢው የወባ በሽታ ከጊዜ ወደጊዜ መጨመር ለጤና እክል፣ ለወጪ እና ለተለያዩ ጫናዎች እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።

በኮንሶ ዞን የካራት ከተማ አስተዳደር የካራት ጤና ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጴጥሮስ ቶሬይቶ፤ ጤና ጣቢያው የካራት ከተማ ነዋሪን ጨምሮ ለአጎራባች ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው ወባን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር ትምህርት እየተሰጠ ቢሆንም ማህበረሰቡ በመዘናጋቱ በሽታው እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል።

የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግርማ ቤሌ፤ በዞኑ ባለፉት 10 ወራት 21 ሺህ 905 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን አብራርተው የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችን ሙሉ በሙሉ በመተግበር ወባን ለመቀነስ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ጠቁመዋል።

በፀረ-ወባ ኬሚካል የተነከረ አጎበርን በተገቢው መንገድ በመጠቀም እና የወባ ትንኝ መራቢያ መንገዶችን በማስወገድ በዞኑ በወባ በሽታ ምክንያት የሚመጣውን ችግር ለመቀነስ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ግርማ ቤሌ አረጋግጠዋል።

የኬሚካል ርጭት በካራትና በሰገን ዙሪያ ወረዳ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፤ የአጎበር አጠቃቀምን በማሳደግ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረ መዘናጋት እና የአጎበር አጠቃቀም ችግር ወባ በዞኑ እንዲጨምር አድርጓል ሲሉም ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን