ለአረጋዊያን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ
በገነት ደጉ
የአረጋዊያን ቀን በየዓመቱ መከበሩ ለአረጋዊያን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የሀዋሳ አረጋዊያን ማዕከል አስታወቀ፡፡
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና መስራች ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በዓሉ በየዓመቱ ስለመከበሩ አስታውሰው፣ ጉዳዩ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አክብረን የምንተወው ሳይሆን በዘላቂነት አረጋዊያንን ለመደገፍ በርካታ ስራዎች የሚሰራበት ነው ብለዋል፡፡
በተለይ አረጋዊያን ለሀገር ትልቅ መስዋትነትን የከፈሉ በመሆናቸው በዘላቂነት ድጋፍ እንደሚያሻቸው ነው ያስረዱት፡፡
ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አረጋዊያን ጡረታ ቢኖራቸውም መጠኑ ዝቅተኛ በመሆኑ መንግስት በቋሚነት በጀት ሊበጅትላቸው እንደሚገባም ነው ዋና ሥራ አስኪያጇ የጠቀሱት፡፡
አረጋዊያን ብዙ እንክብካቤ እና ትኩረት ይሻሉ ያሉት ሲስተር ዘቢደር፣ በሌሎች ሀገራት የአልጋ ቁራኛ ሆነው እቤት ውስጥ ላሉ አረጋዊያን ልዩ ትኩረት፣ እንክብካቤ እና ቤት ለቤት ጉብኝትም እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡
አረጋዊያን ለሀገር የከፈሉትን ዋጋ ያህል በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት አልተሰጣቸውም ያሉት የማዕከሉ መስራቿ፣ እንደ ሀገር ለአረጋዊያን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስታውሰዋል፡፡
የሀዋሳ ሜሪጆይ ኢትዮጵያ ማእከል የአረጋዊያን አስተባባሪ ወ/ሮ እመቤት ተሬሳ በበኩላቸው አረጋዊያን እናቶቻችንና አባቶቻችን የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ጠቅሰው እነሱ ያቆዩትን ሀገር ነው ዛሬ እኛ የምንኖርባት ብለዋል፡፡
እነዚህን አረጋዊያን የመደገፍ እና የመንከባከብ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ያሉት አስተባባሪዋ፣ በርካታ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለእነዚህ እናቶችና አባቶች በተለያየ መንገድ ድጋፋቸውን እያደረጉ ስለመሆናቸው ነው የጠቀሱት፡፡
በዚህም የሀገር ባለውለታዎችን ማስታወስ ችሮታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የሀይማኖት ተቋማት በስራቸው ብዙ ምዕመናን ስለሚገኙ እነሱን በማስተባበር ከአሁኑ በተሻለ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ የገለፁት አስተባባሪዋ፣ የሀይማኖት ተቋማት ትልቁ በጎ ተግባር የሚከናወንባቸው ተቋማት ናቸው በማለት አክለዋል፡፡
አረጋዊያኑ ሀገራችንን መርቀው ማለፍ እንዳለባቸውና መመረቅ ለሀገር በረከት፣ ለምንኖረውም ለእኛም ፀጋ በመሆኑ በዚህም አጋጣሚ አርባ፣ ሙት ዓመት፣ ልደት እንዲሁም ሰርግ እና ኒካ ወደዚሁ ማዕከል በመምጣት አብረዋቸው እንዲያሳልፉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በማዕከሉ ያገኘናቸው አረጋዊ አቶ አለማየሁ ገብረ እግዚአብሔር በማዕከሉ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት መቆየታቸውን ገልፀው በየዓመቱ የአረጋዊያን ቀን ሲከበር በርካታ ሰዎች በመምጣት አብረዋቸው እንደሚያሳልፉ ነው የተናገሩት፡፡
ይህም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የገለፁት አቶ አለማየሁ፣ በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ወገንና አስታዋሽ እንዳላቸው ማሰቡ በራሱ ወደር የሌለው የመንፈስ እርካታ እንደሚያጎናጽፋቸው ተናግረዋል፡፡
ከባሌ ጎባ አካባቢ መምጣታቸውን የገለፁት እኚህ አረጋዊ፣ ልጆች ቢኖሯቸውም ሊጦሯቸው የሚችሉ እና የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ባለመሆናቸው ምክንያት ወደ ማዕከሉ መቀላቀላቸውን አጫውተውናል፡፡
ወ/ሮ ሙሉወርቅ ፀጋዬ በበኩላቸው በማዕከሉ ረጅም ዓመታት እንደቆዩ ጠቅሰው፣ የተሻለ አገልግሎት እያገኙ ስለመሆናቸውም ነው የገለፁት፡፡
ከአረጋዊያን ጋር በርካታ የንግድ ማህበረሰብ እና የተለያዩ የእምነት ተቋማት ምዕመናኖች መንፈሳዊ በዓላትን አብረዋቸው እንደሚያከብሩ አስታውሰው መንግስት ግን እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ትኩረት እንዲሰጣቸውም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው