“ችግር ሊፈትን ይችላል፤ ሊያሸንፍ ግን አይችልም” – መምህር ኢዮብ ትዕዛዙ

በደረሰ አስፋው

ከገጠሩ የአርሶ አደር ማህበረሰብ ነው የተወለደው፡፡ የቤተሰቡም የመጀመሪያ ልጅ፡፡ ከተወለደ ከ4 ወራት  በኋላ ለአካል ጉዳት እንደተዳረገም ከቤተሰቡ ተነግሮታል። ቤተሰብም ወደ ህክምና ተቋም ከመውሰድ ይልቅ አዋቂ ወደ ሚባሉ ሰዎች መውሰድን ነበር የመረጠው፡፡ ፈውስ ግን አላገኘም፡፡ በቀኝ እግሩ ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት ለከፋ ችግር ዳረገው፡፡

ባህላዊና ማህበራዊ ተጽእኖዎች በእሱ ስነ ልቦና ላይ የፈጠሩት ጫናዎች የሚረሱ አለመሆናቸውን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያስታውሳል፡፡ ተጽእኖውና ማግለሉ ከቤተሰብ ከወላጅ አባቱ መጀመሩ ደግሞ ለየት ያደርገዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች የማይመቸው መሰረተ ልማትም ሌላው ጣጣ፡፡ ይሁን እንጂ የትናንቱ ከብት ጠባቂ የተባለው የዛሬው መምህር ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ በሙያው ህዝብንና ሀገርን እያገለገለ ይገኛል፡፡

መምህር እዮብ ትእዛዙ ይባላል፡፡ የተወለደው በጋሞ ዞን ከምባ ወረዳ ገርሰኒቃ በተባለው ቀበሌ ነው፡፡ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ እንደ እድሜ እኩዮቹ መማርን ተመኘ፡፡ ነገር ግን በወላጅ አባቱ የመማር ዕድል ተነፈገ፡፡ ተምረህ ምን ልታመጣ? ይልቁንስ ቤት ውስጥ ቁጭ በል አለያም ከብት ጠብቅ በሚል መመሪያ፡፡

ወላጅ እናቱ ደግሞ የአባትየው ተቃራኒ ሆነው ተሟገቱ፡፡ ጉዳዩን የተረዱት ወላጅ እናቱ የአባትየው ንግግርና ውሳኔ እንቅልፍም ነሳቸው፡፡ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት ጀመሩ። ፊደል ባልቆጠረው አንደበታቸው አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶችን እያነሱ ባለቤታቸውን ለማሳመን ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ አካል ጉዳተኝነት ከመማር የሚገድበው ነገር አይደለም የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ልጄ ተምሮ እኩዮቹ የደረሱበትን ደረጃ ይደርሳል በሚል፡፡ በወላጅ አባቱና እናቱ የተፈጠረው እሰጣገባ ለዛሬው መምህር ኢዮብ መልካም አጋጣሚ ይዞ ብቅ አለ፡፡ የእናቱ መከራከሪያ ሀሳብ ሚዛን ደፋና ምኞቱ እውን ሆኖ ትምህርት ቤት ገባ፡፡

በወላጅ እናቱ ያልተቋረጠ ጥረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር ዕድል አገኘ፡፡ እራሱ ባበጃጃት የእንጨት ምርኩዝ እየተደገፈ የ3 ሰዓት የእግር መንገድ ይጓዝ እንደነበረም ያስታውሳል፡፡

የዓላማ ጽናት ለውጤት ያበቃል የሚለው መምህር ኢዮብ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ነገር በሌለበት አካባቢ እየወደቀና እየተነሳ ላሰበው ደረጃ መድረሱ እንዳስደሰተውም ነው የተናገረው፡፡

ከጊዜ በኋላ ግን የአካባቢው መልክአ ምድር ለአካል ጉዳተኛው ኢዮብ የሚመች አልሆነም፡፡ በተለይ ዝናብ በዘነበ ጊዜ በእግር ተጉዞ መማር ፈተና ሆነበት፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢውንም ለቆ ወደ ከምባ ለመምጣት እንደተገደደም ያነሳል፡፡ ይህም በአንጻራዊነት የተሻለ የመማር ዕድልን ፈጠረለት፡፡ ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በከምባ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተለ፡፡

የትምህርት ቤቱ መምህራንም አካል ጉዳተኝነት ከምንም ነገር እንደማያግድ ያበረታቱት ጀመር፡፡ እንዲያውም ስም ጠሪው የነበሩት መምህር ተሾመ ለአካል ጉዳቱ ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ ማፈላለግም ጀመሩ። ከአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ጋር ለማገናኘት ሀላፊነቱን ወሰዱ፡፡

የማዕከሉ ሰራተኞችም በአካባቢው በመገኘት ለአካል ጉዳተኞች የክራንችና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርጉ መምህር ተሾመም ኢዮብን አገናኙት፡፡ ክራንች ማግኘቱ ቀደም ሲል ከነበረበት እንግልት የሚታደግለት ሆነ። የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በነጻ ማግኘትም አስቻለው፡፡ በዚህም እሰከ 12ኛ ክፍል ካለምንም ችግር ተማረ፡፡

እዮብ ከክራንቹ በተጨማሪ ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍም ከማእከሉ አገኘ፡፡ በወቅቱ በአርባ ምንጭ ተሃድሶ ማዕከል የነበረው እንክብካቤና ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ትኩረት ለየት ያለ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ ከግብአት በተጨማሪ የምግብ፣ የትራንስፖርት ወጪና ህክምና ማግኘቱንም ነው የተናገረው።

በ2006 ዓ.ም የ12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ የሚገልጸው መምህር ኢዮብ፣ የ2ኛ ደረጃ ማጠቃላያ ፈተና ግን የጠበቀውን ዉጤት ማምጣት አልቻለም፡፡ የተመኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግባት ህልሙ በዚሁ ተጨናገፈ፡፡ ኋላም በኮንትራት ቅጥር ህጻናትን ፊደል ማስተማር ጀመረ፡፡ ይህ የስራ ልምድ በመምህርነት ለመወዳደር ዕድል ፈጠረለት፡፡ ወረዳው ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮም ከአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በሂሳብ ትምህርት በዲፕሎማ ተመረቀ። በማስተማርም 9 ዓመት እንደሆነው የሚናገረው ኢዮብ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ለማግኘትም የወራት ዕድሜ እንደቀሩት ያብራራል፡፡

“እናቴ ታሪኬን የቀየረች ናት፡፡ ከብት ጠባቂ የተባልኩት የትላንቱ ኢዮብ ዛሬ ላይ የብዙዎች የቀለም አባት ሆኛለሁ፡፡ ክቡር የሆነውን የመምህርነት ሙያ እንድቀላቀል አድርጋለች፡፡ የትምህርት ቤት መምህራኖቼም ሌላ ጉልበት ሆነውኛል፡፡ በተለይ የክፍል ስም ጠሪ መምህር ተሾመን የምዘነጋቸው አይደሉም፡፡ የአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከልን ድጋፍ ባላገኝ ኖሮ ህይወት እንደዚህ ቀላል አትሆንልኝም ነበር፡፡ ለዚህ የመምህሩን አስተዋጽኦ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ማዕከሉም ቢሆን ለኔ ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ በማድረግ ቆሜ እንድሄድ፣ ስላደረገ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው” ብሏል፡፡

መምህር እዮብ ዛሬ ላይ ትዳር መስርቶ የአንድ ልጅ አባት ሆኗል፡፡ ቤተሰቡንም በዚሁ ስራ በሚያገኘው ደመወዝ ነው የሚያስተዳድረው፡፡ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆንንም በተግባር ኣሳይቷል። በከምባ ከተማም አካል ጉዳተኞችን በአንድ ማህበር ጥላ ስር በማሰባሰብ መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን ማስከበር እንዲችሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡-

“አካል ጉዳት ማለት የአእምሮ ጉዳተኛ መሆን አይደለም፡፡ ዕድሉን ካገኙ ሰርተው መለወጥ ይችላሉ፡፡ መሸከም አልችልም እንጂ ከአቅሜ ጋር የሚጣጣም ስራ መስራት ችያለሁ፡፡ ትልቁን የመምህርነት ሙያን ተቀላቅዬ ተማሪዎቼን በእውቀት በማነጽ የነገው ሀገር ተረካቢዎች እንዲሆኑ የበኩሌን ድርሻ እየተወጣሁ ነው፡፡ ሌሎችም አካል ጉዳተኞች ከልመና ወጥተው እራሳቸውን በስራ መለወጥ አለባቸው፡፡ አልችልም ከሚል አመለካከትም መውጣት አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ተምረው ስራ አጥ የሆኑ አካል ጉዳተኞች ድርብ ችግር ውስጥ በመሆናቸው መንግስት የስራ እድል ሊፈጥርላቸው ይገባል፡፡”

አካል ጉዳተኛ በመሆኔ በህይወቴ የማልረሳው ገጠመኝ አለኝ ሲልም አጫውቶኛል መምህር ኢዮብ፡-

“ወደ ከምባ ከመምጣቴ በፊት ነው ይላል፡፡ ገጠር ከእለታት አንድ ቀን ታይቶ የማይታወቅ ዝናብ ጣለ፡፡ ዝናቡንም በዛፍ ስር ተጠልዬ በተወሰነ መልኩ ማሳለፍ ቻልኩ። ዝናቡ ከተወሰ ጊዜ በኋላ አቆመ፡፡ ወደ ቤት መጓዝ ጀመርኩ፡፡ ከተወሰነ ጉዞ በኋላ ወደ አንድ ወንዝ ደረስኩ፡፡ ወንዙም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል፡፡ ይጎላል ብዬ የጠበኩት ወንዝም እየባሰ በአካባቢው ያገኘውን ነገር እየጠራረገ ይሄዳል፡፡

“ሌላ አማራጭ የምለው ነገር የለምና እዛው መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ የቀኑ ብርሃንም ወደ ጨለማ ተለወጠ፡፡ በዚህ ቦታ እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ ቆይቼ ወደ ቤት መግባት ቻልኩ፡፡ በህይወቴ ልረሳው የማልችለው ገጠመኜ ነው፡፡ ከኔ ጋር የነበሩት ጤናማ አካል ያላቸው የዚህ ችግር ሰለባ አልሆኑም። በፍጥነት በመሄዳቸው ከዝናቡም ሆነ ከወንዙ ሙላት አምልጠዋል፡፡ እኔ አካል ጉዳተኛ ለዚህ ችግር ሰለባ ሆንኩኝ። ይሁን እንጂ በዚህና ሌሎች ችግሮች ተስፋ ቆርጨ አላውቅም፡፡ ይህም ለዛሬው ህይወቴ ማማር አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ችግር ሊፈትን ይችላል፤ ሊያሸንፍ ግን አይችልም”