ጥምረቱ የፍርሃት ወይስ የጥንካሬ?
በፈረኦን ደበበ
ነጻ ሀገራት ቢሆኑም፤ እራሳቸውን ችለው መቆም የተሳናቸው ይመስላል፡፡ በየቀኑ አንዱ ሌላውን ወደ እራሱ ለመሳብ ያማትራል፡፡
የሰሞኑ ደግሞ ከዚህ ሁሉ ያለፈ ነው፡፡ አንዳቸው ለሌላኛቸው እያማተረ የሚውሉትን እርግፍ አድርገው ተዉ፡፡ የብቸኝነት ብዛትና ፍርሃት በርትቶባቸው ይመስላል ተጠራሩ። ሻያቸውንና ቡናቸውን እየጠጡ ጎን ለጎን ለመቀመጥ በቁ፡፡
ለድግሱ አመቺ ተብላ የተመረጠችው ከተማ አሥመራ ስትሆን ጋባዡ ደግሞ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሼክ መሀሙድ ናቸው፡፡ ዋና መልዕክታቸው ደግሞ ከውርደት አድኑኝ፤ አስፈሪ ከሆነችው ኢትዮጵያ ሁላችንም እንዴት እንትረፍ የሚል ነው፡፡
ሥጋትና ፍርሃትን በማስቀረት የጋራ ደህንነትን ለማስጠበቅ እንፈልጋለን ያሉት የሶማሊያ፣ ግብጽና የኤርትራ መሪዎች ተገናኝተው እጅ ለእጅ ተጨባበጡ፡፡ በውስጣቸው ሲመላለስ በቆየው ጉዳይ ላይ ሀሳብ ለሀሳብ የተለዋወጡ ሲሆን ያላቸውን አቅምና ሀብት አቀናጅተው ለመጠቀም ተስማሙ፡፡
ሀገራችን ከማናቸውም ያነሰ ታሪክና አቅም ባይኖራትም ወደ ቀይ ባህር የምታደርገው ግሥጋሴ ግን ፋታ ነስቷቸዋል፡፡ ይህንን ማስቆም የሚቻለው ደግሞ በተናጠል ሳይሆን በጋራ እንደሆነም አምነዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ በባለሥልጣኖቻቸው ሲቀነቀኑ የቆዩ ሀሳቦችንም መልሰው ወደ አዕምሯቸው በማስገባት ተወያዩ፡፡
በመልክዓ – ምድራዊ አቀማመጥ፣ በፖለቲካና በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ግንኙነታቸውን ሲያጠናክሩ የቆዩት ሀገራት ትብብር ግን አሳሳቢ የሚሆነውን ያህል ውኃ የማይቋጥር ገጽታም አለው፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ በራሳቸው ችግር ውስጥ ተዘፍቀው የሌሎችን ድጋፍ የሚጠብቁ እንደመሆናቸው።
የዚህ ዋነኛው ማሳያ እራስን ችሎ ከመቆም ይልቅ በወዳጅ ፍለጋ ላይ መማሰናቸው ሲሆን፥ አቅም አላት የምትባለው ግብጽም ቢሆን ከጦር መሣሪያ ውጭ ጠንካራ የምትባል አይደለችም፤ ምክንያቱም ስትመካበት የነበረው ምጣኔ ሀብቷ በአካባቢው ባለው ጦርነት መነሻ ቁልቁል እየተንደረደረ ስለሚገኝ፡፡
ብዙ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ከሆነ ሁሉ አቀፍ የተባለው ትብብራቸው በቅርቡ ከተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የተገናኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ስብሰባ በኋላ የተካሄደ ሲሆን በሀገራችን ላይ ማነጣጠሩም ተመልክቷል፡፡
በሀገሮቻቸው ላይ የተጋረጠውን የደህንነት ሥጋት የሚያስቀርና የሶማሊያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ያስችላል የተባለው ስምምነት ሦስቱ ሀገራት አንድ ግንባር እንደፈጠሩ የሚያሳይ እንደሆነ ቢገለጽም እያንዳንዱ ሀገር አሁን ካለበት ቁመና አንጻር ግን ይህ ነው የሚል ጥንካሬ የሚያጎናጽፋቸው አይደለም፡፡
የዚህ አንዱ ማሳያ ሁሉም በውስጣቸው ቀውስ ማስተናገዳቸው ሲጠቀስ፥ በተለይ በሶማሊያ የአልሻባብ መጠናከርና ፋታ የማይሰጥ ጥቃት መፈጸሙ እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል፤ የአፍሪካ ህብረት ሠላም አስከባሪ ጦርም ጨርሶ ከሀገሪቱ የሚወጣበት ሁኔታ ሥልጣን ባለው አካል እስካሁን ስላልተወሰነ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መጠጋቷ የደህንነት ሥጋት ይፈጥራል ብለው የሚገልጹት እነዚሁ ሀገራት፤ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ከሶማሊያ ሲወጣ በቦታው ወታደሮቻቸውን የማስፈር ፍላጎት አላቸው፤ ምንም እንኳን አንዳቸውም የቦታውን ተፈጥሯዊ አቀማመጥና የውጊያውን ዘይቤ ባያውቁም፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ብትወጣም እንኳን የሀገሪቱን ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል ገለልተኛ ኃይል መመደብ እየተቻለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግብጽና ኤርትራን በመመደብ ግጭት እንዲባባስ እንደማያደርግም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ኤርትራን ከወሰድንም በውስጧ ያሉት ችግሮችና ሥጋቶች ጠንክራ እንዳትሠራ ያደርጋታል፤ ምክንያቱም በዓለም ላይ ባለው የምጣኔ ሀብትና ፋይናስ ቀውስ መነሻ በችግር ውስጥ ስለምትገኝ፡፡ ባረጀ አስተሳሰብ ውስጥ የሚገኘው የፖለቲካ ሥርዓቱ ያደረሰው ጫናም ህዝባዊ ድጋፉ አስተማማኝ እንዳይሆን ተጽዕኖ ይፈጥርባታል፡፡
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ከሄደች በኋላና አሳዛኝ የነበረው የድንበር ይገባኛል ጦርነቱ ያስከተለውን ጠባሳ ለመሻር መንግሥት ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት የፈረመው የሠላም ስምምነት መልካም ድባብ አምጥቶ ነበር፡፡ ወንድማማችነትን በማስፈን የአብሮነት ስሜትም ፈጥሮ ነበር፤ ምንም እንኳን ያ ግንኙነት ዘላቂ መሆን ባይችልም፡፡
መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት አመርቂ ደረጃ ላይ እንደሆነ ሲገልጽ በቆየበት ሁኔታ የተሰማው ዜና እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም ከወራት በፊት ጀምሮ ሀገሪቱ ከግብጽና ሶማሌ ጋር በመሆን በሀገራችን ላይ ማሴሯን ማንም ያውቀዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ግብጽ የሀገራችንን ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቶችን እያበረታታች የቆየችውን ያህል ጠቃሚ የሚባል አጋር እንድታገኝም አስችሏታል፤ የሀገራችንን “ወዳጅ-ጠላት” የሆነችውን ኤርትራን በመያዝ፡፡ መንግሥት ከህወሀት ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነት መፈጸሙን በመልካም ዓይን ያልተመለከተው የኤርትራ መንግሥትም ተመልሶ ወደ ሤራው መንገድ ገብቷል፡፡
ከታሪክ አንጻር እጥፍ ድርብ አቅሟን እያሳደገች ለመጣችው ሀገራችን ሤረኞች የዘረጉት ወጥመድ ከባድም ቀላልም ሊሆን ይችላል፡፡ ከባድ የሚሆነው መጀመሪያ አንድ ወይም ሁለት ከነበሩበት አሁን ቁጥራቸውን ማሳደጋቸው ሲሆን ረጅም ድንበር በሚጋሩት ሀገራት መፈጸሙም ሥጋቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ሌላው ከሀገራቱ በተጨማሪ በጉያቸው ሌሎች ደጋፊ ኃይላት መኖር መቻል ሲሆን ይህም ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ሎጂስቲካል አቅርቦታቸውን ለማሳደግ ይረዳል፤ የሚገኙበት ፖለቲካዊና መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ጥቅም እንዳለ ሆኖ፡፡
የሦስቱ ሀገራት መሪዎች የፈረሙበት ስምምነት ምን ምን ደካማ ጎን አለው ተብሎ ከተጠየቀም ከአብሮነት ስሜታቸው ባለፈ ሁሉም በምጣኔ ሀብታዊ ችግር ውስጥ መሆናቸው፣ እንደ አልሻባብ ያለ አደገኛ ኃይል ለመጋፈጥ መገደዳቸውና እንዲሁም ኃይልን በሶማሊያ ለማስፈር ህጋዊ መስፈርት ያለማሟላታቸው ሁሉ ተግዳሮት ይሆንባቸዋል፡፡
እነዚህን እንቅፋቶች ለማለፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ ምን ምን ተግባራት ማከናወን አለባት ከተባለም ብዙ ሥራዎች እንደሚጠብቋት ይታወቃል፡፡ የግብጽን የተለመደ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በመገንዘብ ወዳጅ ለማብዛት የጀመርነው ሥራ እንዳለ ሆኖ ይህንን ማሳደግና እስከ ድንበሯ ማጠናከር ጫናዋን ለመቀልበስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በዋለው የህዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ም/ቤት ጉባኤ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ያስቀመጡት የመንግሥት አቅጣጫ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ይህንን አጠናክሮ በተለይ ከሁሉም ሀገራት ጋር ያለንን ግኝኙነት ማሳደግ ተጠባቂ ተግባር ነው እራሳችንን የመከላከል አቅማችንን በየጊዜው ከማሳደግ ጎን ለጎን፡፡ ህብረተሰቡ ነቅቶ በየአካባቢው ችግር ፈጣሪዎችን እንዲከላከል ማነሳሳት ሌላው ተግባር ሲሆን በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተገልጋዩን ማርካትም ሉዓላዊነትን ለማስከበር የምናደርገውን ሥራ ያጠናክርልናል፡፡
የሀገር ግንባታ ሥራውን አጠናክረን ከቀጠልንና ጠላት ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድመን መከላከል ከቻልን የእኛን ብርታት ሰግተው የመሠረቱት ህብረትም ውጤት ማስገኘት ከመቻሉ በፊት ልናፈራርሰው እንችላለን ማለት ነው፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ