በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሣውላ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ በይፋ ተጀምሯል።
የሣውላ ከተማ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤቱን የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳን ጨምሮ ከፍተኛ የክልልና የዞን አመራሮች ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።
የሣውላ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ንጉሴ መኮንን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው፤ የተቋሙ ወደ ዲጂታል አሰራር መቀየር የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ እና የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ፤ ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ሁሉም ዜጋ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አገልግሎትን ያለምንም መድሎ እንዲያገኝ ከማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ነው ብለዋል።
የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ በማድረግ ህዝቡ በዘመናዊ መልኩ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ ብቻ በመክፈል አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፤ ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የማዘጋጃ ቤቱን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደግ ባሻገር ዘመናዊነትን የሚያላብስ መሆኑንና በአጭር ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘመናዊ አሰራርን ካስጀመረች በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሯን ጠቁመው ሣውላ ከተማም የአገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊነት ተቋዳሽ ሆና ለማዘመን የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት መጀመሩ ወደ ላቀ ስኬት መንደርደሪያ በመሆኑ ተደራሽነቱን ማስፋት ተገቢ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
አቶ ጌታቸው ኬኒ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾሙ