በአለምሸት ግርማ
ማልዳ ከእንቅልፏ መነሳት የዘወትር ልማዷ ነው። ጊዜዋን የሚሻማባትን ነገር ለማድረግ አትፈልግም። ይልቁን ስራዎቿን በሰዓት ከፋፍላ ነው የምትተገብረው። ቀኗን የምታሳልፈው በዕቅዷ መሰረት ስራዎችዋን በማከናወን ነው። ማታ ወደ ቤቷ ስትገባ ደግሞ ለነገ የሚያስልጋትን ታዘጋጃለች። ቤተሰቦቿን መጠየቅ፤ ማህበራዊ እና የግል ጉዳዮቿንም አትዘነጋም። የእነዚህ ተግባራት ባለቤት የዛሬዋ እቱ መለኛችን ናት።
ወጣት ነፃነት ምትኩ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ሀዋሳ ከተማ ነው። የ1ኛ ደረጃ ትምህርቷን በሐይቅ ትምህርት ቤት 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች።
የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ከቤተሰብ ጋር አለመግባባት አጋጠማት፡፡ ከቤት ወጣች። ከዚያም ትንሽ ቤት ተከራይታ ያገኘችውን እየሰራች ለመኖር ተገደደች። ወጪዋን ለመሸፈንም ስራ ሳትመርጥ ትሰራ ነበር።
በዚህ መሃል ሀዋሳ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም የተላላኪነት ስራ ተወዳድራ ማግኘት ቻለች። ደሞዙ መጠነኛ ቢሆንም ስራው ቋሚ ስለነበር ተስፋ ፈጥሮላታል። ጎን ለጎንም በተመላላሽ ልብስ ማጠብ እንዲሁም እንጀራ መጋገር፣ የእጅ ስራና የተለያዩ ስራዎችን ትሰራ ነበር።
ከምታገኘው ገቢ በመቆጠብ ትምህርቷን በሒሳብ መዝገብ አያያዝ በዲፕሎማ መርሃ-ግብር መከታተል ጀመረች። ሁለት ዓመታትን ከተማረች በኋላ ግን መግፋት አልቻለችም። ከቆይታ በኋላ በምትሰራበት መስሪያ ቤት የውስጥ ማስታወቂያ ወጣ። የወጣው ማስታወቂያ የሚጋብዛትና የሚጠየቀውን መስፈርት አሟልታ በመገኘቷ በተወዳደረችበት መደብም ፈተናውን በብቃት ማለፍ ቻለች። በዚያ ሁኔታ ከነበረችበት የተላላኪ ስራ መደብ ተነስታ አዲሱ መደብ ላይ መስራት ጀመረች። ገቢዋም የተሻለ ሆነ። ይህም ይበልጥ መነቃቃትን ፈጠረላት።
በኮሌጁ በሚገኘው የኮምፒውተር ላብራቶሪ ውስጥ ስራዋን መስራቷን ቀጠለች። ይህም ከኮሌጁ ማህበረሰብ ጋር የመቀራረብ አጋጣሚ ፈጠረላት።
በዚህ መነሻነት ስራዋን እየሰራች “በላይብራሪ ሳይንስ” ትምህርቷን መከታተል ቀጠለች። ቀን እየሰራች ማታ ትማር ነበር። ይህም ራሷን በሙያዋ ብቁ ለማድረግ ካላት ፍላጎት የመነጨ ነበር። እስከ ደረጃ 4 ድረስ በመከታተል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) ተፈትና ማለፍ ቻለች።
በመቀጠልም አትላስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት በቢዝነስ ማናጅመንት በ2009 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን አገኘች። የወር ደሞዝዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጣ።
በዚህ ሁኔታ እያለች ታዲያ ከምታገኘው ትቆጥብ ነበር። በመስሪያ ቤቷ የማህበር ቤት መደራጀት የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ጊዜ ከቆጠበችው የቁጠባ ማህበር በመበደር በማህበሩ ተቀላቀለች። በህይወቷ ለውጥ የሚመጣ ውሳኔ በመሆኑ ለመወሰን ጊዜ አላባከነችም። የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈልም ቁርጠኛ ነበረች።
በወሰነችው ውሳኔ መሰረት የኑሮን ትግል ለመፋለም ተዘጋጀች። ወጪዋ ጨምሮ ስለነበር በኑሮዋ ላይ ትልቅ ጫና ፈጠረባት። ይህንን ችግር ለመወጣት የሚያስችላት መንገድን ማሰላሰል ጀመረች። በዚህም መሰረት አንድ ነገር ወደ ልቧ መምጣቱን ታስታውሳለች። የስራ አለቆቿ ጋር በመቅረብ ያለባትን ችግር በማስረዳት ስራው በፈረቃ መስራት እንድትችል ፈቃድ ትጠይቃለች። መልካም ፈቃዳቸውን ያልከለከሏት አለቆቿ ከሌሎች ሰዎች ጋር በፈረቃ መስራት እንድትችል ፈቀዱላት። በዚህ ውሳኔ ግማሽ ቀን ከመደበኛ ስራዋ ነፃ መሆን ቻለች።
ያገኘችውን ትርፍ ሰዓት ችግሯን ለመቅረፍ ተጨማሪ ስራ ለመስራት ወሰነች። በዚህም መሰረት በሰው ቤት ተመላላሽነት በ8መቶ ብር ተቀጠረች። ያም ችግሯን በተወሰነ መልኩ ማቅለል አስችሏታል። አንድ ቀን ጠዋት፤ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ከሰዓት እየገባች ስራዋን በትጋት መስራቷን ቀጠለች። በመሃል አሰሪዎቿ የዘመድ ልጅ በማግኘታቸው ስራዋን እንድታቆም ይነግሯታል። ይህም ሌላ ፈተና ሆነባት። ይሁን እንጂ አንዲት ጓደኛዋ በዚያው ሰዓት ምግብ ቤት ውስጥ የፅዳት ስራ አገኘችላት። በምግብ ቤቱ ውስጥ የፅዳት ስራ ለመስራት ብትቀጠርም ስራዋን ስትጨርስ ምግብ ቤት ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን በፈቃደኝነት ታግዝ ነበር። ደሞዟም ከ8 መቶ ወደ 1ሺ5 መቶ ብር ከፍ ስላለ ደስተኛ ሆና ነበር ስራዋን የምትሰራው።
በዚህ ሁኔታ እየሰራች በ“ዩቲዩብ” የተለያዩ የምግብ ስራዎችን ትከታተል ነበር። ያንን እንዲያጠናክርላትም የአጭር ጊዜ የምግብ አዘገጃጀት ስልጠና ወሰደች።
ስልጠናዋን ስታጠናቅቅ የፅዳት ስራውን በመተው በምግብ ዝግጅት ሙያ ተቀጥራ መስራት ጀመረች። መደበኛ ስራዋን በማይነካ ሁኔታ አመቻችታ ስራዋን በመስራት የተበደረችውን ገንዘብ ሳትሳቀቅ መክፈል አስችሏታል። በሁኔታው ኑሮዋን ከመደገፍም አልፋ የሌላ ሙያ ባለቤት መሆን ችላለች። ስራ ያስከብራል የሚል ጠንካራ አቋም አላት።
በዚህ ብቻም አልተገደበችም፡፡ በተጨማሪነት የሴክሬተሪያል ሳይንስ ሙያ በዲፕሎማ ማለትም እስከ ደረጃ 4 በዛየን ኮሌጅ በማታ መርሃ ግብር ተምራ የተመረቀች ሲሆን ይህም አንድ ቀን ሊጠቅማት እንደሚችል አስባ መማሯን አስረድታናለች።
ቀጣይ ዕቅድሽ ምንድነው ብለን ላነሳንላት ጥያቄም እንዲህ ስትል መልሳለች፦
“በሙያዬ ጥሩ ልምድ አግኝቻለሁ። እግዚአብሔር ቢረዳኝ የራሴን ምግብ ቤት ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነኝ። በዚያም ያልተለመዱ አገልግሎቶችን ለማካተት አቅጃለሁ። ማለትም ምግቦችን ቀለል ባለ መልኩ ሰዎች ያሉበት ቦታ በመውሰድ መሸጥ ወይም ማድረስ ነው። ይህም የተሻለ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ። ለእኔም አሁን ካለኝ ልምድና ብቃት ጋር የተመጣጠነ ገቢ ማግኘት ያስችለኛል”
ለችግሯ ጊዜያዊ መፍትሔ ብላ ያሰበችው፤ አሁን ላይ ደስ እያላት የምትሰራው ሙያ ሆኖላታል። ወደፊትም የምታድግበት እንደሆነ እና በዚሁ ጎን ለጎን ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችላት እንደሆነም ትናገራለች።
“ዕቅዴ ራሴን መለወጥ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መትረፍ ነው። ለዚህ ዓላማዬ ደግሞ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ። ደግሞም ጀምሬዋለሁ፤ በቅርቡም እውን አደርገዋለሁ” ብላ የተናገረችው በልበ ሙሉነት ነው።
በቃለ መጠይቃችን ወቅት እንደታዘብነው ከሆነ ትልቅ የስራ ተነሳሽነትና ፍላጎት አላት። የምታገኘውን ገቢም በአግባቡ እንደምትጠቀም አጫውታናለች። ለሰው ልጅ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ብቻውን ስኬታማ እንደማያደርግ፤ ይልቁንም ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉ እንደሚበልጥ የወጣቷ ተሞክሮ ያሳያል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የዕለት ጉርስ ማግኘት ትቸገር የነበረች ሴት አሁን ላይ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ማሰብ መጀመር ችላለች። ወደፊት ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቃት የምትናገረው ወጣት ነፃነት “ለዚህ ያደረሰኝ አምላኬ ነው” ትላለች ደጋግማ።
ሴቶች የተለያየ ፈተና ሊገጠማቸው ይችላል። ነገር ግን ችግራቸውን ሊወጡ የሚገባው ጠንካራ በመሆንና በመስራት ነው። በሚገጥማቸው መሰናክል ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም። ከችግራቸው የሚወጡበት አማራጭ ስራ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል። አንዳንድ ወንዶች የሴቶችን ችግር እንደክፍተት ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። እኔም ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች አጋጥመውኝ ያውቃሉ። ምናልባት ለእንደዚያ ዓይነት ጥያቄዎች ፈቅጄ ቢሆን ዛሬ የደረስኩበት ላልደርስ እችላለሁ። ስለዚህ ሴቶች ለሚቀርቡላቸው የፍቅር ጥያቄ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ጠንክረው ከሰሩ ደግሞ የማይለወጡበት ምንም ምክንያት የለም ስትል ለሴቶች ያላትን ምክር አስተላልፋለች።
ፈተና ጥሎ የሚያስቀረው ተስፋ የሌለውን ካገኘ ብቻ ነው። ምንም በሌለበት ቦታ ላይ ሆኖ ትልቅ ደረጃ መድረስን እያሰቡ መትጋት በእርግጥም የውስጥ ጥንካሬን እና የፈጣሪ እርዳታን ይጠይቃል። ህይወት ሁሌም በትግል የተሞላች እንደመሆኗ ሰዎች ያሰቡበት ለመድረስ ብዙ መሰናክሎችን በጥንካሬ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። እኛም የወጣቷን የህይወት ተሞክሮ በመሰል ጎዳና ያሉ ወጣቶች ሊማሩበት ይገባል ማለት እንወዳለን!
More Stories
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ
“ሁሌም የተሻለ ነገር መስራትና መለወጥ ህልሜ ነበር”