“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ

በአስፋው አማረ

“ሥራ ክቡር ነው” የሚለውን አባባል መርህ በማድረግ፣ ሥራን ሳይንቁ ዝቅ ብሎ በመሥራት ለስኬት የበቁ ሰዎች በርካቶች ናቸው፡፡ የዛሬው ባለታሪካችንም ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የሥራን ክቡርነት በመረዳት የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለ ነው፡፡

አቶ ደረጀ ሞገስ ይባላል፡፡ የኤሊአና ህትመትና ወረቀት ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ትውልድና ዕድገቱ፣ እንዲሁም አሁን ነዋሪነቱን ያደረገው በሀዋሳ ከተማ ነው፡፡

በልጅነቱም ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ፣ በሀዋሳ ታቦር አንደኛ እና ሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ግንቦት ሃያ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡

የመሰናዶ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ዳግመኛ ወደ ሀዋሳ በመምጣት በአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በህግ ትምህርት ክፍል ትምህርቱን በመከታተል በድግሪ ተመርቋል፡፡ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎት አልነበረውም፤ ምክንያቱንም ሲያስረዳን፦
“ሥራ የጀመርኩት በልጅነቴ ነበር፡፡ ሥራ መስራት በጣም እወድ ነበር፡፡ በልጅነቴ ቤት ውስጥ አቅሜ በፈቀደው መጠን የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ቤተሰቦቼን አግዝ ነበር። ሥራ ወዳድነቴን የተመለከተችው እናቴ ትምህርቴን እየተማርኩ ሥራ እንድሰራ እናታዊ ምክሯን ትለግሰኝ ነበር፡፡

“ትምህርቴን እየተማርኩ የሙያ ሥራ እንድሰራ በማድረግ እናቴ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ትምህርት ሲዘጋ ሙሉ ክረምቱን ማሳለፍው በአንድ የእንጨት ሥራ ድርጅት ሙያ እየተማርኩ ነበር፡፡ ሥራውን ስጀምር ክፍያ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን በሳምንት አንድ ቀን የሳሙና እየተባለ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር፡፡

“ይህን የሙያ ሥራ የጀመርኩት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነበር፡፡ ሥራ እየሰራሁ እማር ስለነበር የኮሌጅ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ተቀጥሬ በተመረቅኩበት ሙያ መስራት አልፈለኩም፡፡ በዚህም ምክንያት የራሴን ድርጅት ከፍቼ መስራት ጀመርኩ፡፡

“ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ኮሌጅ ገብቼ እስከምመረቅበት ጊዜ ድረስ ያለማንም እርዳታ ሥራ እየሰራሁ ነበር ራሴን ያስተማርኩት። ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራው ገባሁ” ሲል ይናገራል፡፡

ይህን ተከትሎ ከእንጨት ሥራ ጎን ለጎን የህትመት ሥራ ለመጀመር ፍላጎት እንዳደረበት አጫውቶናል፡፡ የህትመት ሥራውን ከጀመረ በኋላም ትዳር የመሰረተ ሲሆን የባለቤቱ እገዛ ሁልጊዜም እንዳልተለየው ይገልጻል፡፡

የግል ድርጅቱን ከከፈተ በኋላ ከህንጻ ተቋራጭ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የተለያዩ የእንጨት ሥራዎችን መስራት ችሏል፡፡ በሥራው ምክንያት ከቤተሰቦቹ ተለይቶ፥ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በመሄድ ይሰራ ነበር፡፡ በሂደት ግን ከቤተሰቦቹ ርቆ ላለመሄድ ሲል የህትመት ሥራ መስራት ጀመረ፡፡

መጀመሪያ ላይ በአንድ በኩል የፈርኒቸር ሥራውን፥ በሌላ በኩል ደግሞ የህትመት ሥራውን ጎን ለጎን ማስኬድ ጀመረ፡፡ የህትመት ሥራው እየሰፋና እየለመደለት ሲመጣ ግን የእንጨት ሥራውን በመተው “ኤሊአና ህትመት” የተሰኘ ማተሚያ ቤት ከፍቶ ወደ ህትመት ሥራው በስፋት መግባት ችሏል፡፡

የህትመት ሥራውን ሲጀምር ለስራው የሚያስፈልጉ ማሽኖችን በማሟላትና ሙያውንም በማዳበር ወደ ሥራ መግባቱን አውግቶናል፡፡ በሂደት የሥራ አድማሱንም በማስፋት መጽሄት፣ መጽሀፍ፣ ብሮሸር፣ ቢልቦርድ፣ ባነር እና ሌሎች የተለያዩ ሥራዎችን ለመንግስት ተቋማት፣ ለግል እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በቅርብ በኤሊአና ህትመት ከተሰሩ ስራዎች መካከል “የኢትዮጵያ ጀግኖች” የሚል መፅሀፍ በደራሲ ሻለቃ ጳውሎስ ናደው ተዘጋጅቶ ታትሞ ለንባብ የበቃው ይጠቀሳል፡፡

በህትመት ሥራ ውስጥ ከሚገጥሙ ችግሮች ብታጋራን? ብለን ላነሳንለት ጥያቄ ሲመልስ፦
“ሁሉም የሥራ መስኮች ተግዳሮቶች አሏቸው፡፡ ከችግር ነጻ የሆነ የሥራ መስክ አለ ብዬ አላምንም፡፡ የህትመት ሥራ ሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ባለሙያዎች የሚሰራ ነው። በዚህ ጊዜ የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡

“እነዚህ ችግሮች የሚያስከትሉት የገንዘብ ኪሳራ ነው፡፡ ምክንያቱም ለሚባክነው ቁሳቁስ መግዣ የሚውለው ገንዘብና ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ ከ10 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የገንዘብ ኪሳራ ያስከትላሉ፡፡

“ይህ ኪሳራ ሥራ ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ስህተቱን ባለመድገም ቀጣይ ሥራ ላይ ማተኮር ነው የምመርጠው” በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ኪሳራውን ሊያስከትሉ የሚችሉ ባለሙያዎች ደግሞ አንደኛ አዲስ ባለሙያ ሲሆኑና ከልምድ ማነስ ከሚከሰት ስህተት ምክንያት እንደሆነ አቶ ደረጀ አጫውቶውናል።

አሁን ላይ የህትመት ሥራ ላይ ብቻ ነው እየሰራህ ያለኸው? ብለንም ጠይቀነው ነበር፡-
“የህትመት ሥራው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ወደ ‘ኤሊአና ወረቀት ፋብሪካ’ ተሻግረናል። ይህ እድገት የተፈጠረበት አጋጣሚ ደግሞ በህትመት ሥራ ላይ የሚታዩ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግሮች(ክፍተቶች) ስለነበሩ ነው፡፡ ገበያ ላይ ፍላጎቱ ደግሞ ከፍተኛ ነበረ፡፡

“በሌላ በኩል ደግሞ፥ ከአገልግሎት ሰጪነት ወደ አምራች ኢንዱስትሪ መግባት የተሻለ እንደሆነ ስለማምን ነው የኤሊአና ወረቀት ፋብሪካን ለመጀመር ምክንያት የሆነኝ፡፡ አሁን ላይ በቋሚነት እስከ 40 የሚደርሱ ሰራተኞች ተቀጥረው እየሰሩ ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሥራ በሚበዛበት ወቅት በጊዜያዊነት የሚቀጠሩ ሠራተኞች አሉን፡፡

“አሁን ላይ ድርጅቱ በዋናነት እያመረተ የሚገኘው የተለያዩ የፕሪንተር ወረቀቶችን ነው፡፡ ለአብነት A4 እና A3 ወረቀቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፥ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ካርዶችን ማለትም፥ እንደ ክላስተር (ዶሴ) እና ለሆስፒታል አገልግሎት የሚውሉ የካርድ ምርቶች ይገኙበታል” በማለት ይናገራል፡፡

“ችግሮች ሁሌም ይኖራሉ” የሚለው ባለታሪካችን፣ ባደግን ቁጥር አይነታቸው ይለያይ እንጂ ችግሮች ዓይነታቸውንና ይዘታቸውን እየቀያየሩ እንደሚከሰቱ ይናገራል፡፡ “ነገር ግን ችግሮች አሉ ብለን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም።” ይላል፡፡ “ችግር ሥራ ያስቆማል” ብሎ አያምንም፡፡ ይልቁንም ለችግሩ መፍትሄ በማፈላለግና ቀጣይ ሥራዎችን እንዴት መስራት አለብን የሚል አስተሳሰብን ማዳበር ይቻላል ሲል ሃሳቡን ያጠናክራል፡፡

“አሁን ላይ እየተጠቀምንባቸው የሚገኙ ማሽኖች ከፍተኛ የመብራት ሀይል፣ የማምረቻ ቦታና ሌሎችንም የተለያዩ ለሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በአንድ ላይ ለማግኘት ትልቅ ተግዳሮት ነበረ፡፡ ይህ ደግሞ ማሽኑ ሳይሰራ ከሁለት ዓመት በላይ ለሥራ አመቺ ቦታ በመፈለግ ጊዜ ባክኗል” ሲል ገጥሞት የነበረውን ተግዳሮት አጋርቶናል፡፡

ይሁንና መንግስት ጉዳዩን በተገቢው መንገድ በማጤን በተለይም ደግሞ የሚፈጥረውን የሥራ እድል ታሳቢ በማድረግ፥ የማምረቻ ቦታ በማመቻቸት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁሞ፥ በዚህም በተሻለ ሁኔታ በማምረት ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በቀጣይ ደግሞ ሥራውን አስፍቶ በመግባት የሰራተኛ ቁጥሩን በማሳደግ እና ከውጭ የሚመጡ ጥሬ እቃዎችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራን የመስራት እቅድ እንዳለው አጫውቶናል፡፡

በርካታ ሰዎች የተለያዩ የሥራ ዕቅዶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዶች ግን ሥራ ሳይጀምሩ ችግሮችን በመፍራትና በመዘርዘር ወደ ሥራ ሳይገቡ ይቀራሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ ነው የበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕቅዶች መክነው የቀሩት፡፡ ነገር ግን ወደ ሥራ ገብተን ለሚገጥሙን ችግሮች መፍትሄ በማፈላለግ ወደ ህልማችን መገስገስ ይኖርብናል” በማለት ምክረ ሀሳቡን ይሰነዝራል፡፡

“በዚህ የሥራ እንቅስቃሴ ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የምትይዘው ባለቤቴ ናት፡፡

በሥራ ላይ ገንቢ ሀሳቦችን በማቅረብና የእኔንም ሐሳብ ተቀብላ አንድ ላይ በማቀናጀት ብሎም ሀሳቦችን በማዳበር ለሥራችን ስኬት ከፍተኛ ሚና አላት” በማለት ስለባለቤቱ ይናገራል፡፡

“በዚህ ሁሉ ሂደት ልምዴን፣ ጉብዝናዬንና አቅሜን አልተማመንም፡፡ በነገር ሁሉ እግዚአብሔር በብዙ አግዞኛል፡፡ ምክንያቱም ከእኔ በብዙ የተሻሉ እያሉ እኔ እዚህ ደርሻለሁ። ከዚህም በኋላ በእርሱ በመታገዝ ብዙ ርቀት የመሄድ ህልም አለኝ፡፡ ነገሮች በጅምር ያልቀሩት እግዚአብሔር ስለረዳኝ ነው” በማለት አምላኩን አመስግኗል፡፡