ማርቲን ኦዴጋርድ ለአንድ ወር ያህል ከሜዳ ይርቃል
የአርሰናሉ አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ በጉዳት ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ከሜዳ እንደሚርቅ ተገልጿል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ የመሀል ሜዳ ተጫዋች በ7ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መርሐግብር በለንደን ደርቢ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር በተካሄደው ጨዋታ ጉዳት ማስተናገዱ ይታወሳል።
በዚህም ጉዳት የተነሳ ማርቲን ኦዴጋርድ እስከቀጣዩ የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ወይም እስከ ህዳር 9/2018 ድረስ ወደ ሜዳ ላይመለስ እንደሚችል ቢቢሲ አስነብቧል።
በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ኖርዌያዊው አማካይ መድፈኞቹ በፕሪሚዬር ሊጉ ከፉልሃም ፣ ክርስቲያል ፓላስ፣በርንሌይና ሰንደርላንድ እንዲሁም በሻምፒዮንስ ሊጉ ከአትሌቲኮ ማድሪድ እና ስላቪያ ፕራህ ጋር የሚያከናውኑት ጨዋታዎች የሚያመልጡት ይሆናል።
የ26 ዓመቱ ተጫዋች በዚህ የዉድድር አመት በጉዳት እየተፈተነ ይገኛል፡፡
ተጫዋቹ በፕሪሚዬር ሊጉ ከሊድስ ዩናይትድ፣ኖቲንግሃም ፎረስት እና ዌስታሀም ጋር መድፈኞቹ በተገናኙባቸዉ ያለፉት 3 ተከታታይ ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ከእረፍት በፊት ተቀይሮ ከሜዳ መዉጣቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ በ3 ተከታታይ ጨዋታዎች በመጀመሪያዉ አጋማሽ ተቀይሮ ከሜዳ የወጣ የመጀመሪያዉ ተጫዋች ሆኗል፡፡
ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ሞሮኮ አሜሪካን በማሸነፍ ለግማሽ ፍፃሜ ደረሰች
ኤርሊንግ ሀላንድ 50 ጎሎች ላይ ፈጥኖ የደረሰ ተጫዋች ሆነ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያካሂዳል