በርካቶችን ከድካም የሚታደግ የፈጠራ ውጤት
አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስከ 20 ሊትር ውሃ በቀላሉ ከጉድጓድ መሳብ የሚያስችል የፈጠራ ስራ ቴክኖሎጂ ባለቤት ወጣት አማኑኤል ኤልያስ የምህንድስና ባለሙያ ነው።
በ2010 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቅ ነው::
ትውልድ እና እድገቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ ሲሆን ለፈጠራ ስራውም በአከባቢው የሚስተዋለው የውሃ ችግር መነሻ እንደሆነው ገልጿል::
በቅርበት ከሚያገኛቸው ቁሳቁሶች የፈጠራ ስራ የሰራው ወጣት አማኑኤል ችግር ፈችነቱ ተረጋግጦ የፈጠራ ባለቤትነት በአእምሯዊ ጥበቃ ባለስልጣን ምዝገባ እንደተደረገለትም ተናግሯል።
በአማካይ በሰው ጉልበት በአንድ ደቂቃ በቀላሉ እስከ 20 ሊትር ውሀ መቅዳት የሚያስችለው የፈጠራ ስራዉ ጊዜንና ጉልበትን ከመቆጠቡ በተጨማሪ ከንክኪ የጸዳ በመሆኑ የውሃው ንጽህናም እንዲጠበቅ የሚያደርግ እና ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጫናም ይቀንሳል ብሏል።
ከጉድጓድ ውሃ በቀላሉ መሳብ የሚያስችለው ይህ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ሪቨርስ ኦስሞሲስ(Reverse Osmosis) በሚባለው ቀመር ሲሆን ያም ማለት ከዝቅተኛ ቦታ ወደ ከፍተኛ ቦታ ግፊትን በመጠቀም ውሃን መሳብያ ቀመር ነው ሲልም አብራርቷል።
የውሃ መሳብያ ፓምፑ ከአንድ አመት በላይ በሙከራ አገልግሎት ላይ ውሎ የተፈተሸና ውጤታማ የሆነ ስራ እንደሆነም በመግለጽ ከ10-15ሜትር ርቀት ላይ ያለ የጉድጓድ ውሃንም ለመሳብ በቀላሉ እስከ ስምንት ሺህ ብር የሚፈጅ የፈጠራ ስራ እንደሆነም ወጣቱ ተናግሯል።
በዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት ክፍል አሰልጣኝ የሆነው ወጣት አማኑኤል ኤልያስ የፈጠራ ስራውን ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ እንዳለ እንዲሁም በግሉ ከዚህ ፈጠራ ስራው ጋር በተያያዘ ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም በሌላ የፈጠራ ስራ ማለትም ለግንባታ አገልግሎት የሚውል በአንድ ጊዜ አምስት የአፈር ጡብ ማምረት የሚያስችል ማሽን ሰርቶ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ላይ እንዳለም ተናግሯል።
የዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ድረስ በተለያዩ የትምህርትና የሙያ መስኮች ተማሪዎችን ሲያበቃ የቆየ ኮሌጅ እንደሆነ የኮሌጁ ምክትል ዲን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሙየዲን አብደላ ገልጸዋል።
አክለውም በኮሌጁ የህብረተሰቡን ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች በማስፋፋት ረገድ ከተከናወኑ ስራዎችም ለአብነት ተንጠልጣይ የብረት ድልድይ ፣የእንጨት መሰንጠቅያ ቴክኖሎጂ ፣ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ዘመናዊ የዶሮ ቤት፣ የንብ ቀፎ፣ ጉልበት ቆጣቢ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ እና የተለያዩ ፈጠራዎች የታከሉባቸው የቤት እና የቢሮ እቃዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው የፈጠራ ስራዎች በኮሌጁ ተሠርተው እንዳሉም ነው የገለጹት አቶ ሙየዲን።
ዘጋቢ: ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስፋፋት የእርባታ ስራውን ምርታማነት የማሳደግና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አፈር አልባ የመኖ አመራረት ዘዴን አስተዋወቀ
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ እንድናስመዘግብ ረድቶናል – በቤንች ሸኮ ዞን የሸይ ቤንች ወረዳ አርሶአደሮች