የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ እንድናስመዘግብ ረድቶናል – በቤንች ሸኮ ዞን የሸይ ቤንች ወረዳ አርሶአደሮች
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ እንድናስመዘግብ ረድቶናል ሲሉ በቤንች ሸኮ ዞን የሸይ ቤንች ወረዳ አርሶአደሮች ተናገሩ።
ምርምር ማዕከሉ ከወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የማዳበርያ አጨማመርና ያመጣውን ለውጥ በተመለከተ የመስክ ጉብኝት አድርገዋል።
የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኮሙኒኬሽን ምርምር ስራ ሂደት አስተባባሪና የማዕከሉ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ማረኝ አለሙ ማዕከሉ በግብርና አዲስ የወጡ ቴክናሎጂዎችን የማላመድ የማስተዋወቅ እና የኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴዎችን አርሶአደሩ ተግባራዊ እንዲያደርግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።
ማዕከሉ በክልሉ በሚገኙ 4 ዞኖች ማለትም በካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች የተለያዪ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ያሉት አቶ ማረኝ በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ocp በተሰኘ ፕሮጄክት ድጋፍ በክልሉ በሚገኙ 2 ወረዳዎች ይህን ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማዕከሉ የተፈጥሮ ሃብት ምርምር ዳይሬክተር ወይዘሮ ቆንጂት አብርሃም ይህ ተግባር በወረዳው በሚገኙ የ18 አርሶአደሮች ሰርቶ ማሳያ ላይ የተከናወነ መሆኑን እና አርሶአደሩም ይበጀኛል ያለውን የግብዓት አጠቃቀም በተግባር እንዲለይ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሮጄክቱ ዋንኛ አላማ የአርሶአደሩን የግብአት አጠቃቀም ግንዛቤ በማስፋት ምርትና ምርታማነት አንዲጨመር መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ቆንጅት በዚህም ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በአርሶአደሩ ሰርቶ ማሳያ ላይ የተለያዩ የማዳበርያ አይነቶችን በስድት ፕሎቶች በመከፋፈል ግብአቶችን በመጠቀም የተስተዋሉ ለውጦችን አርሶአደሩ አንዲገነዘብ ማድረግ መቻሉን በማዕከሉ የአፈር ለምነት ተመራማሪ አቶ በላይ ታደሰ ተናግረዋል ።
የአርሶአደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሻሻል የተለያዩ ግብአቶችን በመጠቀም በተግባር የተከናወነውን ስራ ለማስፋት ይሰራል ያሉት ደግሞ የሸይ ቤንች ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት የዕርሻና ህብረት ስራ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ወንድይፍራው ወዳጆ ናቸው።
ከወረዳው አርአደሮች መካከል አርሶአደር ጌታሁን ተሰማና ጴጥሮስ ሞላ፤ ከዚህ ቀደም ሰፊ ማሳ ላይ ቴክኖሎጂን ሳይጠቀሙ እንደሚያለሙ ገልጸው የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በማሳቸው ላይ የሰጠው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስልጠና በብዙ መልኩ እንደረዳቸው አንስተዋል።
በቀጣይም በተለያየ መልኩ በተግባር የተጣቸውን የግብአት አጠቃቀም በማስፋት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል ።
ዘጋቢ፡ ትዕግቱ ጴጥሮስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በርካቶችን ከድካም የሚታደግ የፈጠራ ውጤት
“ከቆቦ ዛፍ የተሽከርካሪ ነዳጅን መፍጠር የቻለው” – ወጣት ታሪኩ አዳነ
ምርታማነት በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ቢሮ ገለጸ