የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማን ዉብ፣ ሳቢና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዳዉሮ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ

የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማን ዉብ፣ ሳቢና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዳዉሮ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ

በዞኑ ታርጫ ከተማ እየተከናወነ ባለዉ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠቃሚ መሆናቸዉን ሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸዉ ወጣቶች መካከል ወጣት ዮሐንስ ባሳ እና አቶ አግዜ አፍቴ ገለፀዋል።

ወጣትቹ ይህም ብቻ ሳይሆን ከተማን ዉበትን በማላበስና ገጽታን በመቀየር በኩል የኮሪደር ልማት ፋይዳዉ የጎላ ነዉ ብለዋል።

በ4.6 ሚሊየን ብር ወጪ 1ኛ ሎት የኮሪደር ስራ 2 ሺህ 85 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የመናፈሻ ቦታዎች፣ ሳር እና ችግኝ ተከላን ጨምሮ በርካታ ተግባር አልቆ ወደ 2ኛዉ ሎት መገባቱን የታርጫ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደለ አበራ ገልፀዋል።

በዚህም በቋሚነትና በጊዜያዊነት ከ1 መቶ 36 በላይ ወጣቶች ሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የአካባቢዉን ገጽታ መቀየር መቻሉንም አቶ ታደለ ተናግረዋል።

በታርጫ ከተማ የተጀመረዉ ኮሪደር 1 ከዉበት፣ ለነዋሪዎች ምቹ ከመሆን፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከተማን ከማነቃቃት አንፃር ፋይዳዉ የጎላ መሆኑን የገለፁት የታርጫ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ባትሳ ወንድሙ፤ ከወጣቶች ማዕከል እስከ መሀል ከተማ ቃለ ህይወት ቤቴክርስቲያን ድረስ የኮሪደር 2 ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በተለይም በከተማዋ እየተሰራ ያለው ጌጠኛ የእግረኛ መንገዶች፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችና ሌሎች የከተማዋን ገጽታ እየቀየሩ መሆናቸዉን አብራርዋል።

በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ ስራ በዞኑ ለሚገኙ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩንም አቶ ባትሰ አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከተማው ከወጣቶች ማዕከል እስከ ድረስ የአንድ ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን ውል ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ አራት ሜትር ስፋት ያለው ጌጠኛ የእግረኛ መንገድ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ መናፈሻዎችና ሌሎች ግንባታዎችን እንደሚያካትት አቶ ባትሳ አስረድተዋል።

ይህ ለነዋሪዎች ምቹ የሆነና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለዉ የኮሪደር ልማት በሁሉም ከተማ አስተዳደሮች የማስፋፋት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥሉ የዳውሮ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ተረፈ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አባይነሽ ወራቦ – ከዋካ ጣቢያችን