“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ

“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ

በአለምሸት ግርማ

ተፈጥሮ ከለገሰቻቸው የእናትነት ኃላፊነት በተጨማሪ በተሰማሩበት የሙያ መስክ አሻራቸውን ያሳረፉ ሴቶች በርካታ ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት ሴቶች ከጥቅማቸው ይልቅ የሙያ ፍቅርን የሚያስቀድሙ ሲሆን ለቤተሰባቸው፣ ለአካባቢያቸው እንዲሁም ለሀገራቸው ጉልህ ሚና በማበርከት ይታወቃሉ። ተምሳሌትነታቸው የሚጀምረውም ከዚሁ ነው። የዛሬዋ እቱ መለኛችንም በሙያዋ በርካቶች የሚያደንቋት በደቡብ ኤፍኤም 100.9 ላይ ከነበሩ መስራች ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ነች።

ተወልዳ ያደገችው በይርጋለም ከተማ ሲሆን ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ናት። በልጅነቷ ደራሲ የመሆን ፍላጎት እንደነበራትም አጫውታናለች። በዚህም ምክንያት ለቋንቋ ትምህርት ትኩረት ታደርግ ነበር። በተማረችባቸው ትምህርት ቤቶች መምህራኖችም ያበረታቷት ነበር። በወቅቱ በትምህርት ቤት ውስጥ ተግባቢና የጎላ ተሳትፎ የነበራት ተማሪ ነበረች። ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ።

የ1ኛ ደረጃ ትምህርቷን በራስ ደስታ ዳምጠው ትምህርት ቤት፤ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በይርጋለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለችው። የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ሃዋሳ በመምጣት በሃዋሳ ቤተሰብ መምሪያ በበጎ አድራጎት ስራ የወጣቶች የአቻ መምህር በመሆንና በሌሎች መስኮችም ተሳትፋለች። ጎን-ለጎን የስነ-ፅሑፍ ስራዎችንም ትሰራ ነበር። በወቅቱ በደቡብ ንጋት ጋዜጣ ላይ የሚሰሩ የምታውቃቸው ሰዎች ስራዎቿ በጋዜጣው ለህትመት እንዲበቁ ያደርጉላት ነበር።

በዚህ መሃል ነበር የደቡብ ሬዲዮ በ1997 ዓ.ም ምስረታውን ተከትሎ የስራ ማስታወቂያ የወጣው። በተለያዩ ስራዎቿ የሚያውቋት ሰዎች እንድትወዳደር መረጃውን ያደርሷታል። እሷም በውስጧ የነበረውን ፍላጎቷን የምታወጣበት አጋጣሚ ስለነበር የደረሳትን መረጃ ችላ አላለችም። መስፈርቱን ታሟላ ስለነበር ተመዘገበች። በዘርፉ የተዘጋጁ የተለያዩ ፈተናዎችን በብቃት አለፈች። በስራዋ ጅማሬ የሬዲዮ ዜና ማንበብ፣ ፕሮግራሞች ማዘጋጀት እና የተሰጣትን ስራ ሁሉ በትጋት ትወጣ እንደነበር በቅርበት የሚያውቋት የስራ ባልደረቦቿ ይመሰክራሉ።

በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ቀጠለ። የሚቀርቡ የሬዲዮ ፕሮግራሞችም ብዙ አድማጭ መሳብ ቻሉ። በክልሉ የመጀመሪያ ሚዲያም ስለነበር ተወዳጅነት አገኘ። “በተለይም በወቅቱ ትኩስ ጉዳይ የነበረው በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚያጠነጥን “የዘመኑ ጥሪ” በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ሰፊ ስራዎችን ሰርታለች። ብዙ ሰዎችም ፕሮግራሙን ይወዱትና ይከታተሉት ነበር”

“በወቅቱ የነበረው የስራ ድባብ ደስ ይል ነበር።መድከም መሰልቸት አይታሰብም። ትኩረታችን ስራው ላይ ብቻ ነው። አብዛኞቻችን በልምድ የገባን ጀማሪ ጋዜጠኞች ብንሆንም በወቅቱ የነበሩ ፕሮግራሞች በአድማጭ ዘንድ ተቀባይነት ነበራቸው። ለሙያው ከነበረን ፍቅር የተነሳ በትጋት ነበር የምንሰራው። ወጣትነቱም የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው።” ስትል የነበረውን ሁኔታ ታወሳለች፡፡

“በዚህ ሁኔታ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በድርጅቱ አገልግያለሁ። በኋላም በተፈጠረ አጋጣሚ ስራዬን እየወደድኩት ለመልቀቅ ተገድጃለሁ።

“ስራዬን ለቅቄ ሌላ ስራ በማፈላልግበት ወቅት ሜሪ ጆይ እኔን የሚጋብዝ አንድ ማስታወቂያ ወጣ። በዚያም ተወዳድሬ በማለፌ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። በሜሪጆይ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል ውስጥ በተመደብኩበት ስራ ማገልገል ቀጠልኩ። ቀስ በቀስም ስራው ከህይወቴ ጋር ተዋሃደ። ስለተቀጠርኩ ብቻ ሳይሆን ስራውን የራሴ አድርጌ ነበር የምሰራው። ወቅቱ የማዕከል ግንባታ የተጀመረበት ስለነበር ተደራራቢ ስራዎችን ነበር የማከናውነው። በተለይ ሃብት ከማሰባሰብ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ ብዙም ያልተለመደ ስለነበር ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ ነበር ትኩረት አድርገን የሰራነው። በትምህርት ቤቶች፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በማህበራዊ ተቋማት እና መሰል ስፍራዎች በመገኘት እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ነበር ስራውን የምናከናውነው በሀብት ማሰባሰብ ስራ ላይ በሃዋሳም ሆነ በአዲስ አበባ ለዚህ ስራ ጠይቄው ፊቱን ያዞረብኝ ማንም የለም። በዚህ አጋጣሚ በወቅቱ በቀናነት ለደገፉን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ ስትል በአፅንኦት ተናግራለች።

“በተለይም ከታዋቂ አርቲስቶች ጋር በመሆን ሀብት ስናሰባስብ አንዳንዶች እነሱ ፊት የገቡትን ቃል መፈፀም ይከብዳቸውና እኛን የሚያለፉበት አጋጣሚም ይፈጠር ነበር። የሚከፈለኝ ክፍያ ከስራው ጋር ተመጣጣኝ አልነበረም። እንደአጋጣሚ ሆኖ ሁለቱንም ልጆቼን የወለድኩት እዚያ እየሰራሁ በነበረበት ወቅት ነው። ከስራው ባህሪ የተነሳ በቂ እረፍት አላደረኩም። ህመም ገጥሞኝም ነበር። ተኝቼ እንኳን በስልክም ጭምር የምሰራበት አጋጣሚም ነበር። ያንን የማደርገው በወቅቱ የስራው ጉዳይ ከህይወቴ ጋር በመዋሃዱ እና ስራው ትኩረት ይፈልግ ስለነበር ነው። በልጅነቴ ወላጅ እናቴ ለሰዎች በተለይም አቅም ለሌላቸው ሰዎች መድረስን እያስተማረች ነው ያሳደገችኝ። እናቴ ሰዎችን ማገዝ ትወድ ነበር። የታመመ ስትጠይቅ፤ ካላት ስታካፍል እመለከት ነበር። ያ ድርጊት በውስጤ ተቀርፆ ስለነበር ስራውን የምሰራው በፍላጎት ነበር።

በተለይም ተጠቃሚ የነበሩ አረጋዊያን የሚሰጡን ፍቅርና ምርቃት ስራውን በትጋት እንድሰራ አድርጎኛል። በብዙ ድካም ማዕከሉ ተገንብቶ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ሲደረግ በጣም ተደስቻለሁ። ምክንያቱም ማዕከሉ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል በዙሪያው ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። ያንን ፈተናዎች በማለፍ ለሚገባቸው ሰዎች አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ትልቅ ደስታ ነበር የተሰማኝ። ማዕከሉ ብዙ መስዋዕትነት የከፈልኩበት ስለሆነ እንደመጀመሪያ ልጄ ነው የማየው።

“በቆይታዬ ብዙ ተግዳሮት የገጠሙኝ ቢሆንም አንድ አሻራ ማሳረፍ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ስራው ብዙ ትዕግስትን የሚጠይቅ በመሆኑ በሴትነቴ ያንን በብቃት በመወጣቴ ደስተኛ ያልነበሩ ሰዎች የተለያየ ተግዳሮት ሲፈጥሩብኝ ቆይተዋል። ነገር ግን እኔ የራሴ ዓላማ ስለነበረኝ የሚጠቅመኝን አስተያየት እንጂ አሉታዊ ነገሮችን ወደ ውስጥ አላስገባም ነበር። ያም ዓላማዬን ከግብ እንዳደርስ ረድቶኛል። በጋዜጠኝነትም ሆነ በሜሪጆይ በነበረኝ ቆይታዬ ብዙ ልምድ ቀስሜያለሁ። ብዙ ወዳጆችንም አፍርቼበታለሁ፡፡”

“ከቆይታ በኋላ ስራው ላይ ሌላ ባለሙያ መተካት ስለነበረበት እና ለቤተሰቤም በቂ ጊዜ መስጠት እንዳለብኝ በማመኔ ስራውን ለማቆም ወሰንኩ። በእርግጥ ቀላል አልነበረም። ለመልቀቅ ከወሰንኩኝ በኋላ በተለይም በዚያ ካሉ አረጋዊያን ፍቅር ለመለየት ከብዶኝ ነበር። በዚህ ሁኔታ ከቆየሁ በኋላ በ2016 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ስራዬን አቁሜያለሁ።

ለ15 ዓመታት እንደቤተሰብ ከተዋሃደችበት የስራ ቆይታ በኋላ ሜሪጆይ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከልን በመልቀቅ አሁን በግል ስራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።

ስለምትሰራው ስራዋ ስትናገር፦

“በቆይታዬ ያገኘሁት ልምድ ለዛሬ አቅም ፈጥሮልኛል። ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ያካበትኩትን ልምድ በመያዝ ነው። አሁን ላይ በፕሮሞሽን ስራ ተሰማርቼ “ህይወት ፕሮሞሽን” በሚል ስያሜ እየሰራሁ እገኛለሁ። ስራዎቼ መድረክ መሪነት፣ ኢቭንት ኦርጋናይዘር፣ ዶክመንተሪ ፊልም፣ የሬዲዮ ፕሮዳክሽን፣ ስልጠና ማስተባበር፣ በራሪ ወረቀቶችንና ሌሎች የህትመት ስራዎችን ማዘጋጀት፣ የድርጅቶችን ማህበራዊ ሚዲያ፣ ማስተዳደር፣ የሀገር ውስጥ ፈንድ ማፈላለግና ገቢ ማሰባሰብ ዝግጅቶችን ማማከርና ማዘጋጀት ይገኙበታል። በጅምር ላይ ብሆንም በቀጣይ እየተጠናከረ የሚሔድ ስራ ነው። “ከብራይት ኦቲዝም ማዕከል” ጋር እንዲሁም “ከጣሊታ የህፃናት ማሳጊያ” ጋር በጋራ የእግር ጉዞን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን አከናውኛለሁ።

በተጨማሪም የሴት ጋዜጠኞች ማህበር የሃዋሳ አስተባባሪ በመሆንም እያገለገለች ትገኛለች። በቀጣይም በተለይም ከሴቶች ጋር በተያያዘ ከሙያ አጋሮቿ ጋር መስራት እንደምትፈልግ አጫውታናለች።

ለሴቶች እንዲህ ስትል ትመክራለች፦

“ሴቶች በየትኛውም ቦታ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። ነገር ግን ለሚገጥማቸው ፈተና እጅ መስጠት የለባቸውም። እኔ ለፈተናዎቼ ተሸንፌ ቢሆን ስራዬን ትቼ ቤት ተቀምጬ ነበር የምገኘው። ወደ ኋላ የሚጎትተኝን ነገር ትቼ ትኩረቴን ስራዬና ዓላማዬ ላይ በማድረግ ዛሬ ላይ መድረስ ችያለሁ። ስለዚህ ሴቶች ያሰቡበት ለመድረስ ከፈለጉ በተለይ ለአሉታዊ አስተያየቶች ቅርብ መሆን የለባቸውም” ስትል ትመክራለች፡፡