ባለፉት ጊዜያት በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከሩ ተግባራት መከናወናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ
ሀዋሳ፣ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ጊዜያት በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከሩ ተግባራት መከናወናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገልጿል፡፡
“በአጋርነት የዳበረ ኮሚዩኒኬሽን ለህዝብ እምነትና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ከሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ጋር የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተደረገ ይገኛል።
በመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበትና የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት በተጀመረበት ማግስት መከናወኑ መድረኩን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በእነኚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ስራዎች የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል።
በዚህ መነሻ ባለፉት ጊዜያት በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከሩ የህትመት፣ የማህበራዊ ሚዲያ፣ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የብልጽግና ጉዞን እውን የሚያደርጉ የዘርፉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በተለይም በድህረ-እውነት ዘመን የሀሰት የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችን እና ህዝብን ከአመራሩ የሚያጋጩ የሀሰት መረጃዎችን ለማስቀረት ፈጣንና በመረጃ የበለጸገ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይም የህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመረኮዘ፣ የሀሳብ የበላይነትን ያረጋገጠ የሚድያና ኮሚዩኒኬሽን ስራን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አቶ የሺዋስ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ ሀገራችን ኢትዮጵያ የማንሰራራት ጊዜ ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ አማራጮች መረጃዎች በተበራከቱበት በዚህ ወቅት የዘርፉ ስራዎች ህዝብንና መንግስትን በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
አብሮነትን የሚሸረሽሩ ከፋፋይ አጀንዳዎችን ማስወገድ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ነጋ፤ ስራዎቻችን ከመደመር እሳቤ የተቀዱ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በቀጣይም ብልጽግናን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በህዝብና መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
አቶ ጌታቸው ኬኒ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾሙ
የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማን ዉብ፣ ሳቢና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዳዉሮ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ
የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍን በቤት ሙከራ በማስደገፍ ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ