እየተባባሰ የመጣውን የወባ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ከስርጭቱ ፍጥነት አንፃር ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ

እየተባባሰ የመጣውን የወባ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ከስርጭቱ ፍጥነት አንፃር ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ

ጨቅላ ህፃናትንና እናቶችን ጨምሮ በህብረተሰብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የመከላከያ ዜዴዎችን በንቃት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በወረዳው ዶዕሻ ከተማና ደዳ ቀበሌ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

በሀዲያ ዞን ለወባ በሽታ ተጋላጭ ከሆኑ ወረዳዎች መካከል የሻሾጎ ወረዳ አንዱ እንደሆነ ተመላክቷል።

በወረዳው ዶዕሻ ከተማና ደዳ ቀበሌ ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢው የነበረው የወባ በሽታ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑና ብዙዎችንም ለአልጋ ቁራኛ እንዳደረጋቸው አስታውቀዋል።

የጤና ተቋማት በበሽታው በተጠቁ ታማሚዎች የመጨናነቅ አዝማሚያዎች እንደሚስተዋሉ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህም በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የመድኃኒት እጥረት እንዲያጋጥም መንስኤ ስለመሆኑም አውስተዋል።

ህብረተሰቡ በሽታውን አስቀድሞ የመከላከያ ዜዴዎችን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ቸልተኝነት መኖሩን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ የኬሚካል ርጭት በበቂ ሁኔታ አለመኖር እና የአልጋ አጎበር ስርጭት መቋረጥ ስርጭቱን እንዳባባሰው አስረድተዋል።

በዶዕሻ ጤና ጣቢያ የመድሀኒት ክፍል ባለሙያ ጌዲዮን ኤርሚያስ እና በተቋሙ የላብራቶሪ ክፍል ባለሙያ ሁሴን አኖሴ በየበኩላቸው በበሽታው ሳቢያ ወደ ተቋሙ የሚመጡ የታማሚዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ይህም የመድኃኒትና ሌሎች የመከላከያ ኬሚካሎች እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በሀድያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ባቾሮ፤ የወባ በሽታ በወረዳው ባሉ በሁሉም ቀበሌያትና ከተሞች በስፋት መሰራጨቱን ገልፀው ከእነዚህም ውስጥ 56 ከመቶ በዶዕሻ ክላስተር እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ንቅናቄዎች ተፈጥረው የጤና ባለሙያዎች በማሰማራት ቤት ለቤት ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ጨቅላ ህፃናትንና እናቶችን ጨምሮ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያስከትለው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመከላከያ ዜዴዎችን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ግብዐት በማቅረብ የበኩላቸውን እንዲወጡ ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅረበዋል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን