ከህክምና ባለሙያዎች ጥሩ አገልግሎት እያገኘን ቢሆንም በመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለው ችግር ሊቀረፍ ይገባል ሲሉ በሀዲያ ዞን ሆመቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያነጋገርናቸው የወባ በሽታ ታካሚዎች ገለጹ

ከህክምና ባለሙያዎች ጥሩ አገልግሎት እያገኘን ቢሆንም በመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለው ችግር ሊቀረፍ ይገባል ሲሉ በሀዲያ ዞን ሆመቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያነጋገርናቸው የወባ በሽታ ታካሚዎች ገለጹ

የግቤ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት በበኩሉ እየተስፋፋ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል ቅንጅታዊ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የወባ ስርጭት በመስፋፋቱ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ጤናን እየተፈታተነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ከወረዳው ሰዴ፣ ቸቾ እና ገሰደ ቀበሌያት በወባ በሽታ ተይዘው ወደ ሆመቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመምጣት ተኝተው ሲታከሙ ያገኘናቸው ወ/ሮ መሠረት መላኩ፣ ታመነች አረጋ እና ልጃቸውን በማስታመም ላይ የነበሩ አቶ ታደሰ ኤርጫፎ እንደተናገሩት፤ ወደ ሆስፒታሉ ከመጣን ወዲህ በሀኪሞቹ ዘንድ ጥሩ እገዛ እያገኘን ቢሆንም እየተስተዋለ ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ግን ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል።

የበሽታው መስፋፋት የጤና እክል ከመሆኑም ባሻገር የኢኮኖሚ አቅማችንንና የማህበራዊ ህይወታችንን በጫና ውስጥ እያስገባ ነው የሚሉት ታካሚዎቹ በመንግሥት በኩል ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል።

በሆስፒታሉ የሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር በረከት ደሳለኝ፤ የወባ በሽታ ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑን አንስተው በተለይም ካለፈው አንድ ወር ወዲህ የታየው የወባ ምርመራ ውጤት ከፍተኛ መሆንኑን ገልፀዋል።

የጤና ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት የህክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የሚናገሩት የሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን በአንዳንድ የመድሃኒት አይነቶች ላይ እጥረት መኖሩን በተላይም በመርፌ መልክ የሚሰጠውን መድኃኒት በቀላሉ ማግኘት አዳጋች ስለመሆኑ አንስተው ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በአንድ ጊዜ ብርድ ብርድ የማለትና ሙቃት የመቀላቀል፣ የእራስ ምታት መሰማት፣ የመገጣጠሚያዎች ህመምና የመሳሰሉት ምልክቶች የወባ በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ እነዚህ ምልክቶች የታዩባቸው ወገኖች ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ እንደሚኖርባቸው ያሳሰቡት ዶ/ር በረከት በሽታው በጊዜ መታከም ካልተቻለ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ነው ብለዋል።

የግቤ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የበሽታ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ትዕግስቱ ጥላሁን በበኩላቸው፤ እየተስፋፋ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመግታት የህክምና አገልግሎት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ቅንጅታዊ የመከላከል ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በወረዳው ካሉት ከ25 መዋቅሮች በአስሩ ቀበሌያት የበሽታው ጫና ከፍተኛ መሆኑን በዕለታዊና ሳምንታዊ ሪፖርት መለየት መቻሉን ተከትሎ ህብረተሰቡን በመከላከያ ዘዴ ዙሪያ የማስገንዘብ ስራ ከመስራትም ባሻገር ለወባ መራቢያ በሚጠረጠሩ ቦታዎች ላይ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ ትዕግስቱ አያይዘውም መንግስት ከዚህ ቀደም ለአምስት አመት አገልግሎት እንድሰጥ በማሰብ ለህብረተሰቡ ያቀረበው የአልጋ አጎበር ከተሰራጫ ገና ሶስት አመቱ ቢሆንም አንድ አንድ ግለሰቦች ላልተገባ ዓላማ እንደሚገለገሉበትም አንስተዋል።

በሽታው በተላይ ነፍሰጡር እናቶችንና ህጻናትን በቀላሉ የሚያጠቃ በመሆኑ የአልጋ አጎበር ቅድሚያ ተሰጥቶ መገልገል ተገቢ ነው ያሉት አቶ ትዕግስቱ በአልጋ አጎበር አጠቃቀም ልዩነት በበሽታው የመያዝ ዕድልን የሚያሰፋ እንደሆነ በዳሰሳ መለያት መቻሉን ነው ያስታወሱት።

አሁን ላይ ያለው የአየር ጠባይ ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ በመሆኑ እስከ ታህሳስ ወር ማለቂያ ድረስ የሚቆየው ሁለገብ የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ከመድኃኒት አቅርቦትና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ “ፈጣን ምላሽ ሰጭ ኮሚቴ” በሚል ተዋቅሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡም ገዳይ የሆነውን የወባ በሽታ ለመከላከል ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን ፈጥኖ በማፋሰስና የአካባቢውን ንጽሕና በመጠበቅ እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራሱን መከላከል እንደሚገባው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን