በደረሰ አስፋው
ከውቦቹ አባያና ጫሞ ሀይቆች መገኛ፣ የጋሞ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ውቢቷ አርባ ምንጭ ነው የፈለቀችው፡፡ የሽመና ጥበብ እምቅ አቅምን ወደ ውጤት በመለወጥ ከራስ አልፎ ሀገርን ለመለወጥ ከሚታትሩ እንስቶች መካከል ተጠቃሽ ነች፤ የዛሬዋ ባለታሪካችን፡፡
በአርባ ምንጭ ከተማ ስንቀሳቀስ “ነጺ የባህልና ዘመናዊ ልብስ ስፌት” የሚል ታፔላ ተመለከትኩ፡፡ ወደ ስራ ቦታዋ ጎራ አልኩና እጅግ ጠቃሚ የሚባል የህይወት ክህሎትን ከራሷ አንደበት ማዳመጥ ቻልኩ፡፡ የታታሪነት ምሳሌ ነች፡፡ ጥሩም ይሁን መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ሀብት በመለወጥ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን አቅምን ገንብታለች፡፡ ተሞክሮዋን እንድታጋራን ቀጠሮ ይዤ ተለያየን፡፡
በቀጠሮ ሰዓት ሥራ ቦታዋ ስደርስ በስራ ተጠምዳለች፡፡ በሙያው ከተሰማራች ከ4 ዓመታት በላይ እንደሆናት ነገረችኝ፡፡ “በነፂ ባህላዊና ዘመናዊ ልብስ ስፌት” በውጭና ውስጥ በተለያዩ ዲዛይንና ቀለማት የተዘጋጁ ዘመናዊና ባህላዊ አልባሳት ተሰቅለዋል፡፡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ብቻ ሳይሆን ለስብሰባ ብለው የሚመጡ እንግዶችን የገበያ መዳረሻ ለማድረግ ትጥራለች፡፡
ጊዜው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ህዝቡን ያስጨነቀበት፤ ሁሉም ቤቱን ዘግቶ የተቀመጠበት ነበር፡፡ እሷ ግን ይህን ጊዜ ለመልካም ተጠቀመችበት፡፡ ውጭ ከሚገኙ ባለሙያዎች በኦን ላይን ለ2 ወር በቀሰመችው ዕውቀት ከሙያው ጋር መገናኘቷን ትናገራለች። በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በስራ ያካበተችውን ልምድ አዋህዳ ሀብት ፈጥራበታለች፡፡
ከስልጠናው ማግስት በ200 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የጀመረችው ዘመናዊና ባህላዊ አልባሳት ስፌት አድጎ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ባለቤት አድርጓታል፡፡ በአንድ ትንሽ ሱቅ የጀመረው ስራዋም አድጎ ወደ ሁለት ቅርንጫፍ አድጓል፤ የወንዶችና የሴቶች በሚል፡፡ ከ25 ሰው በላይ የስራ ዕድል ፈጥራለች፡፡ በብትን ጨርቅ አስመጭነት ተመዝግባ ከዱባይ፣ ቱርክ፣ ህንድና ቻይና በማምጣት ለሌሎች ታከፋፍላለች፤ ለራሷም ትጠቀማለች፡፡ በዚህ ብቻ ያልተገታው የባለታሪካችን ነጻነት ካሳሁን ትጋት በቅርቡ የሽመና መሳሪያዎችን ተክላና ባለሙያዎችን ቀጥራ የሽመናውን ዘርፍ በማዘመን በሀገርና በውጭ ያለውን ገበያ ለመጠቀም ወደ ተግባር ምዕራፍ ላይ ደርሳለች፡፡
የሶስት ልጆች እናት መሆኗን የገለጸችልኝ ነጻነት ስራው ቤተሰቧን ለመምራትም እንከን አልፈጠረባትም፡፡ ጊዜዋን በአግባቡ እንደምትጠቀም በመግለጽ፡፡ በትምህርቷም ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ 2ኛ ማስተርስ ይዛለች፡፡ በስራዋም በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በመስራት የካበተ ልምድን አዳብራለች፡፡ በነዚህ የስራ ቆይታዋም ሌሎችን እያሰለጠነች እሷም ሁነኛ ልምድን መቅሰሟ ለዛሬው የንግድ ስራዋ መሰረት እንደጣለላት ነው ያወጋችኝ፡፡
ወ/ሮ ነጻነት ካሳሁን የተወለደችው በጋሞ ዞን ጨንቻ ከተማ ነው፡፡ ከህጻንነት ዕድሜዋ ጀምሮ መኖሪያዋ ያደረገችው ግን አርባ ምንጭ ከተማ ነው፡፡ ከመሰል እኩዮቿ ጋር አፈር ፈጭታ ጭቃ አቡክታ እቃቃ ተጫውታ እንዳደገች ታወሳለች። ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በአባያ 1ኛ ደረጃ እስከ 8ኛ ክፍል፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡
የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተናን ጥሩ ውጤት በማምጣት ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ አቅንታ በሶሻል ወርክ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲም በኤዱኬሽናል ሳይኮሎጂ 2ኛ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪዋን እንዳገኘችም በመንግስት መስሪያ ቤት በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ተቀጥራ በአንድ ማዕከል የኢንተርፕራይዞች ስልጠና ክፍል ኦፊሰር ሆና ለ3 ተከታታይ ዓመታት ሰርታለች፡፡ ለወጣቶች ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት፣ ስልጠና መስጠትና ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመገናኘት ተበዳሪ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማብቃት ስራ ትሰራ ነበር፡፡
መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅቶች (ዩኒሴፍ እና ዶት ኢትዮጵያ) ውስጥ ለወጣቶች፣ ለመንግስት ሰራተኞች፣ ለተማሪዎች የቢዝነስ ፕላን ዝግጅት፣ የኮምፒውተር ስልጠና እና የህይወት ክህሎት ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን የማጎልበት እና ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ትሰራ እንደነበር ነው የገለጸችው፡፡
በዩኒሴፍ ውስጥ በቆየችባቸው የ2 ዓመታት አገልግሎት ቆይታዋም ወጣት ጥፋተኞች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታረሙና ለሀገር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ስልጠናዎችን በመስጠት የበርካታ ጥፋተኛ ወጣቶች እናት በመሆን ጉልህ ሚና ስለማበርከቷ ይነገርላታል፡፡ ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 14 የሚገኙ በመሆኑና ወደ ማረሚያም የማይገቡ ጥፋተኞች ለአልባሌ ህይወት እንዳይዳረጉ በማስቻል የህይወት ክህሎት ስልጠናው አስፈላጊ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ ለአመታት ያገለገለችው ነጻነት በነዚህ ዓመታትም የሌሎችን ህይወት ከመለወጥ ባሻገር እሷም ልምድ ያገኘችበትና በርካታ ቁም ነገሮችን የቀሰመችበት እንደነበርም ታነሳለች፡፡ ማስልጠን ብቻ ሳይሆን አብሮ መሰልጠንም ያለበት የስራ ቆይታዋ በርካታ ዕውቀት የገበየችበት ነበር፡፡ ወደዚህ ስራ ለመሰማራት ቀድሞም የሙያው ዝንባሌ ቢኖራትም አሁን ለተሰማራችበት የሙያ መስመርም መነቃቃትን እንደፈጠረላት በመጠቆም፡፡
አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ አዳማ፣ ሀዋሳና ሌሎች ከተሞች ተዘዋውራ ስትሰራ ከየአካባቢዎቹም ብዙ ተሞክሮዎችን የቀሰመችበት በመሆኑ ወደ ቢዝነሱ ለመግባት እንዳነሳሳት ነው የተናገረችው፡፡ “ሁሌም የተሻለ ነገር መስራትና መለወጥ ህልሜ ነበር” ምትለው ነጻነት፤ እነሆ ዛሬ ላይ ይህ ህልሟ እውን ሆኖ በለውጥ ጎዳና ላይ እየተንደረደረች ስለመሆኑ ነው የገለጸችልኝ፡፡
ወላጅ አባቷ በመምህርነት እንደሚያገለግሉ፤ እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት መሆናቸውን ገልጻ ስራው ከወላጆቿ ያገኘችው ልምድ አለመሆኑን ነው የተናገረችው፡፡ ዛሬ ላይ የሷን ፈለግ የተከተሉ በዲግሪ የተመረቁ ወንድምና እህቶቿ ጭምር ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የልብስ ዲዛይንና ስፌት ስልጠና በመውሰድ አብረዋት ይሰራሉ፡፡ ለእነሱም የስራ እድል መፍጠሯ ደስተኛ አድርጓታል፡፡
ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳትን በማዘጋጀት የበርካታ ደንበኞች ባለቤት ሆናለች፡፡ በአራት ዓመታት የልብስ ስፌት ስራዋ ልምዷን እያዳበረች መሄዷ ተመራጭ አድርጓታል። በዘመናዊ አልባሳት ስፌት ለተመራቂ ሴቶች፣ ለሙሽሮች፣ የወንድ ሱፎችን፣ የሴቶች ባህላዊና ዘመናዊ ቀሚሶችን ታዘጋጃለች። የሀበሻ አልባሳትን በመስፋትም የስራዋን አድማስ እያሰፋች ትገኛለች፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሰማራት የሽመና መሳሪያን በመትከል የሀበሻ ቀሚሶችን፣ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አልባሳት በሽመና ለማምረት ትኩረት እያደረገች እንደምትገኝ ነው የተናገረችው፡፡ የባህላዊ አልባሳት ፍላጎት ማደግ ደግሞ ስራው ይበልጥ አዋጭ እየሆነ ስለመምጣቱ ታነሳለች፡፡ ጋቢ፣ መነን፣ ነጠላ የጥበብ ግብአቶች በማቅረብና በመሸጥ ጭምር ነው የተሰማራችው፡፡
ነጻነት የማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ዓላማ በማዋል በቀሰመችው ዕውቀት ለውጤት እንዳበቃት ነው የተናገረችው፡፡ በዓለም ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ በነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በቤት ወስጥ ቁጭ ብላ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ይህን አጋጣሚ ግን ወደ መልካም ዕድል ለወጠችው፡፡ የልብስ ስፌት ማሽኖችን በመግዛት በቤት ውስጥ የልጆች፣ የቤተሰብና የቅርብ ጓደኞቿን ልብሶችን በመስፋት ይበልጥ አቅሟን የምታጎለብትበትን መንገዶችንም ተከተለች፡፡
በ200 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል 2 ማሽኖችን እና ብትን ጨርቆችን ገዛች፡፡ አነስተኛ ቤት ተከራየች፡፡ ስራዋ እያደገ መጣና የተከራየችው ቤት ጠበባትና ሌላ ተጨማሪ ቤት ተከራየች፡፡ ተጨማሪ ሰራተኞችንም ለመቅጠር ተገደደች። ዛሬ ላይ ነጻነት በኦዲት የተረጋገጠ መረጃ ባይኖራትም በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብትና ንብረት ባለቤትም አድርጓታል፡፡
በሽመና ስራው ላይ ሰፋ ያለ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ በሀገርና በውጭ ያለውን የገበያ ዕድል ለመጠቀም ማሽኖችን በመግዛት ላይ እንደሆነች ነው የተናገረችው፡፡ ይህም ምርቱን ከአዲስ አበባ በማስመጣት ይደርስባት የነበረውን እንግልትና መዘግየት በመቅረፍ ደንበኞቿን ለማርካት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ታነሳለች፡፡
በስራው ከተሰማራሽ በኋላ አመጣሁ የምትይው ለውጥ ምንድነው? ብለን ላነሳንላት ጥያቄ ስትመልስ፡-
“ለውጥ ሲባል እንደየሰዉ አመለካከትና እይታ ይለያያል፡፡ በስራህ እርካታ መፍጠሩ አንዱ ነው፡፡ ኑሮህን በአግባቡ መምራቱም እንዲሁ ለውጥ ነው፡፡ ያሰብከውን በማሳካት ረገድ ሌላው ለውጥ ነው ብሎ የሚያስብ አለ፡፡ ይሁን እንጂ እኔ አመጣሁት የምለው ለውጥ ቢኖርም ገና ነው፡፡ እስካሁን መድረስ የሚገባኝ ቦታ ደርሻለው የምለው ደረጃ ላይ አልደረስኩም። ይሁን እንጂ ከመንግስት ስራ ወጥቶ እራስን ችሎ ሀብት ንብረት አፍርቶ ያሰቡት ደረጃ ላይ ደርሶ ልጆች ወልዶ አሳድጎ ማስተማር በራሱ ትልቅ ለውጥ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡
“በህይወቴ ባገኘሁት ልምድም ለሴቶች የምለው አለ፡፡ ከቤት እንዲወጡ እመክራለሁ። ከጠባቂነት መንፈስ መውጣት የመጀመሪያው ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ነጻነታቸውን እራሳቸው ማረጋገጥ አለባቸው። መስራት በሚገባቸው ዕድሜ ላይ ያለውን እድል ሊጠቀሙም ይገባል፡፡ ዕድሜ ከገፋ በኋላ ለቁጭት እንዳይጋለጡ እድሜያቸውን በውጤት ማጀብ አለባቸው፡፡ በቤት ውስጥ ልጅ ከማሳደግ ጎን ለጎን መስራት ይቻላል፤ መማርም ይቻላል፡፡
“እኔ የመንግስት ስራ እሰራ ነበር፡፡ በትርፍ ሰአቴ በግል ኮሌጆች እና በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አስተምር ነበር፡፡ 2ኛ ዲግሪ ትምህርቴንም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እማር ነበር፡፡ በቤትም 3 ልጆቼን እንከባከብ ነበር፡፡ አልችልም የሚል መንፈስ በውስጤ አልነበረም። ባል በሚያመጣው ብቻ ይበቃኛል የሚባልበት የጠባቂነትን ዘመን ከአእምሯቸው ሊያወጡ ይገባል፡፡ ትዳር መመስረትና ልጅ መውለድ የህይወት ማብቂያ አድርገው መመልከትም የለባቸውም፡፡ ካገቡ በኋላም ሌላ ህይወት እንደሚቀጥል መገንዘብ ይገባል፡፡
“በህይወቴ ላይ የፈጣሪን እገዛ አልዘነጋውም፡፡ ስንፍናን ፈጣሪም አይወድም። በላብህ በወዝህ ብላ ነው የሚለው፡፡ ትንሽ ጥረት ባደረኩ ቁጥር እንደሚያግዘኝ እምነቱ አለኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያገለገልኩባቸው መንግስታዊና መንግስራዊ ያልሁኑ ድርጅቶች ላይ ያካበትኩት ልምድም በህይወቴ ላይ ላመጣሁት ለውጥ በጎ ተጽእኖ አሳድሮብኛል። በተለይ “ዶት ኢትዮጵያ” ላይ የሰራሁባቸው ጊዜያት የተለየ አቅም የፈጠርኩበት ነበር፡፡ ስልጠናዎችን ስወስድ የተሻለ ነገር እንዳስብና ባለራዕይ እንድሆን አግዞኛል፡፡ ያለኝ ነገር በቂ ነው ብዬ እንዳልቀመጥ አድርጎኛል፡፡
መመህር የሆኑት አባቷም በሷ ህይወት ላይ ያሳደሩባትን በጎ ተፅዕኖ የምትዘነጋው አይደለም፡፡ መማር፣ መስራት፣ ማደግን ይመኙ እንደነበር በማስታወስ ሴት ልጅ አግብታ በቤት ውስጥ መቀመጥ እንደሞት ነበር የሚቆጥሩት፡፡ ይህንንም የህይወት ስንቅ ይመግቧት እንደነበር ነው ያነሳቸው፡፡
“ስኬት ጠንክሮ መስራት፣ የቅንነት እና የጽናት ድምር ውጤት ነው” እንዳለው እውቁ ፈላስፋ አርስቶትል፣ ባለታሪካችን ወ/ሮ ነጻነትም የህይወት ተሞክሮም በጽናት ጠንክሮ በመስራት ያመጣችው ስኬት ነውና ሌሎችም ከዚህ እንዲማሩ ተመኘን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው