በደረሰ አስፋው
“ከቤተሰቤ የወረስኩት ነገር የለም። ወደ ሰማይ ባንጋጥጥ የሚመጣልኝ ነገር እንደሌለም ተገነዘብኩ፡፡ ስር ከሰደደ ችግር የመውጫው መንገድ ትምህርት ነው አልኩ። ወደ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ትምህርቱም ቢሆን ከመማር በዘለለ ያመጣልኝ ለውጥ የለም፡፡
“ስራ በማፈላለግ ብዙ ቦታዎችን ወጣሁ ወረድኩ፡፡ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ደጆችን ጠናሁ፡፡ ከአቀባበላቸው ጀምሮ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡት ቦታም ዝቅተኛ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት ለአካል ጉዳተኞች የሙያ ስልጠና ይሰጣል የሚል መረጃ ደረሰኝ፡፡
“ስልጠናው ወደ ሚሰጥበት ሀዋሳ ተግባረእድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አቀናሁ። ተመዝግቤም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ማምረት የሚሰጠውን ስልጠና ለአንድ ወር ያህል ተከታትዬ በሰርተፊኬት ተመረቅኩ፡፡ ከስልጠናው በኋላ ግን ባለቤት የሌለን ሰዎች ሆንን፡፡
“ከስልጠናው ባሻገር ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ድጋፍ አድርጎ ወደ ስራ ሚያስገባን አካል አጣን፡፡ የቀሰምነው ስልጠናም የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ ቀረ፡፡
አንዳንዶች ወደ ቀድሞ ልመናቸው፤ አንዳንዶች ወደ መጡበት የገጠሩ መንደር፣ አንዳንዶች ደግሞ ወደ ተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማሩ፡፡ የእኔም እጣ ፈንታ ያ ሆነና በጫማ ማሳመር ስራ ተሰማራሁ” ሲል ነው ንግግሩን የጀመረው፡፡
ተሻለ ዮሃንስ ይባላል፡፡ በጫማ ማሳመር (በሊስትሮ) ስራ ላይ እያለ ነበር አግኝተን ያነጋገርነው፡፡ ወላጅ ቤተሰቦቹን በሞት ያጣው ተሻለ ከትውልድ አካባቢው ወደ ሀዋሳ የመጣው የተሻለ ስራ አገኛለሁ ብሎ ነበር። ግን አልሆነም፡፡ ያም ቢሆን አሁን የተሰማራበት ስራም እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ እለት እለት ከስፍራው አይታጣም፡፡
ትውልድና እድገቱ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሸበዲኖ ወረዳ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዚሁ በወረዳው በሚገኝ ትምህርት ቤት ከ1ኛ ደረጃ እስከ 2ኛ ደረጃ ተምሯል፡፡ አሁን ደግሞ በዩኒክ ስታር ኮሌጅ በማርኬቲንግ የትምህርት ዘርፍ ዲፕሎማውን እየተከታተለ ይገኛል፡፡
በተፈጥሮ ሁለቱ እግሮቹ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ነው የተወለደው፡፡ ተሻለ ለወላጆቹ የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ ከእሱ በታች 4 ታናናሾች አሉት፡፡ አካል ጉዳቱ ቤተሰቡን በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው እንደበር ያስታውሳል።
ወደ ህክምና ተቋም አቅንተው ለአካል ጉዳቱ መላ ካለው ብለው ነበር፡፡ ከአካባቢው ህክምና አለፍ ብለውም የተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ አቅንተውም ነበር፤ እንዳሰቡት ግን አልሆነም፡፡
አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። አካላዊ ብቃትን በሚጠይቁ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በማህበረሰቡ ውስጥ በሚኖራቸው የእለት ተዕለት መስተጋብር የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል፡፡
የስነ ልቦና ጉዳት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩም ይችላሉ። እንደዚያም ሆኖ ከማህበረሰቡም ሆነ ከተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ታግለው ለአካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም አርአያ የሆኑ ተጠቃሽ አካል ጉዳተኞች ጥቂት አይደሉም።
ተሻለ ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳለፋቸው ጊዜያቶች ለዚህ አንዱ ማሳያ ናቸው። አቅመ ደካማ ቤተሰቦቹ እርሱን ሰው ለማድረግ የከፈሉትን ዋጋ በማንሳት ራሱን በራሱ ለማሸነፍ የተጓዘበትን ርቀት እንዲህ ሲል ይገልጻል፡-
“እኔ በጣም ትልቅ የተባለውን የችግር ህይወት ተጋፍጬ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ የነበሩበት ዝቅተኛ የአኗኗር ህይወት ለችግሬ መጉላት ምክንያት ነበር፡፡ በዚህ ላይ የእኔ አካል ጉዳተኛ ሆኖ መፈጠር ‘በቁስል ላይ እንጨት. . . ’ እንደሚባለው ነበር የሆነብኝ፡፡”
ይሁን እንጂ ተሻለ እስከ ዕድገቱ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች እንዲያሸንፍ ሁሌም ከጎኑ የነበሩት ወላጅ አባቱን ዛሬም አልዘነጋቸውም። አባቱ ሽኮኮ እያሉ እየወሰዱት ትምህርት እንዲጀምር ያደረጉትን ጉልህ አስተዋጽኦ መቼም አይዘነጋውም፡፡
በትምህርት ቤቱ የነበረውን ቆይታም ምንም እንኳ ያሰበው ደረጃ ባያደርሰውም ለዛሬው ህይወቱ መሰረት የጣለለት መሆኑን አልዘነጋም። ባይማር ኖሮ እስካሁን ድረስ በገጠር ተደብቆ ይኖር እንደነበር በመገመት፡፡
በሀዋሳ ተግባረ እድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች በጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ ማምረትና ጥገና ስራ አጭር ስልጠና ወስዶ በሰርተፊኬት ተመርቋል፡፡ ስልጠናው እጅግ ጠቃሚና ውጤታማ ሊያደርግ እንደሚችል ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡
ሰርተፊኬት ብቻ ግን ስራ ሊሆን አይችልም። ትልቁ ነገር አካል ጉዳተኞችን ከልመና የሚያወጣ ድጋፍ እንጂ፡፡ ከስልጠናው በኋላ የግብአትና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግለት ባለማግኘቱ ስራውን መስራት አልቻለም፡፡
የቆዳ ውጤቶች ስራ ከራስ አልፎ ለሀገር ሊጠቅም የሚችል የስራ ዘርፍ እንደሆነም ያነሳል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን በመጠቆም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አካል ጉዳተኞችን አምራች ሀይል በማድረግ ከተመጽዋችነት በማላቀቅ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ይረዳል፡፡ በዘርፉ በሀገር ውስጥ ያለውን የገበያ እድል መጠቀሙም በርካቶችን ከድህነት ሊያወጣ የሚችል እንደሆነም ያነሳል፡፡
ይሁን እንጂ ተሻለ ከስልጠና በኋላ በራሱ አቅም ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማግኘት አዳጋች ሆኖበታል፡፡ በገበያ ላይ ውድ መሆናቸውም ሌላው ፈተና ነበር። ብድር ለማግኘት ወደ አበዳሪ ተቋማት ቢሄድም የአሰራሩ ውስብስብነት ተስፋ እንዳስቆረጠው ይናገራል፡፡ በዚህ ላይ ብድር እንኳ ለማግኘት በአበዳሪ ተቋማት አካባቢ ከሚሰሩ አካላት ጋር ትውውቅን የሚፈልግ ሆኖ እንደተመለከተውም ነው የተናገረው፡፡
ከስልጠናው በኋላ የት ደረሳችሁ የሚላቸው በመጥፋቱ ግማሹ ተመልሶ ለልመና ተዳርጓል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ባላቸው ነገር የተለያዩ ስራዎች ላይ መሰማራታቸውን ያነሳል፡፡ እሱም ቢሆን ይሄ እጣ ፈንታ ነው ያጋጠመው፡፡
ተስፋ አድርጎት የነበረው የቆዳ ስራ ተሳክቶ ቢሆን ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችል ይናገራል፡፡ ወደ ስራ እገባለሁ ብሎ ተስፋ ቢያደርግም “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን አላይ” እንደተባለው ሆኖብኛል ያለው ተሻለ፥ በሰለጠነበት የስራ ዘርፍ አለመሰማራቱ ቁጭት እንደፈጠረበት ነው ያነሳው፡፡
ወጣት ተሻለ አሁን የህይወቱ መተዳደሪያ ያደረገው የጫማ ማሳመር ስራ (ሊስትሮ) ነው። ወላጅ አባቱንና እናቱን በሞት የተነጠቀው ወጣቱ አርሶ ጎተራ የሚከተው አሊያም ነግዶ የሚያተርፈው ጥሪት የለውም።
ህይወቱን የሚደግፍ ከጎኔ የሚለው እንደሌለም ያነሳል፡፡ ለእሱ ከእሱ ውጪ አለኝ የሚለው የለም፡፡ አካል ጉዳተኛ ነኝ አልችልም ሳይሆን ችሎ በማሳየቱና ሰርቶ ራሱን መለወጥ በመቻሉ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡
“ሰርቼ መለወጥ እንጂ ለምኜ መብላት አልሻም፡፡ አካል ጉዳተኛ ነኝ፡፡ አካል ጉዳቴን ተጠቅሜ መለመንን አስቤው አላውቅም። በርካታ ሙሉ አካል ያላቸው ሲለምኑም እመለከታለሁ፡፡ ‘እጅና እግር እያላቸሁ ማየት ምትችሉበት አይን እያላችሁ፣ ጤናማ አእምሮ እያላችሁ መለመናችሁ ነውር ስራ እየሰራችሁ ነው’ በማለት እመክራቸዋለሁ፡፡ በዚህም ብዙ አካል ጉዳተኞች ከመለመን ይልቅ መስራት እንዲችሉ በማድረግ ወደ ስራ የተሰማሩ አሉ።” ይላል።
በተፈጥሮ በሁለቱ እግሮቹ ላይ የደረሰበት የአካል ጉዳት ለመንቀሳቀስ አዳጋች ቢሆንበትም ራሱ ባዘጋጀው ጫማ መሳይ ነገር ሁለቱም የእግር መዳፎቹ ላይ ጠቅልሎ ይንቀሳቀሳል። ከሊስትሮ ስራው ጎን ለጎን የካልሲና ሌሎች ቁሳቁሶችን አስቀምጦ መስራት ቢያስብም በአቅም ማነስ እንዳልተሳካላት ይናገራል። አሁን ብቸኛ ስራው ጫማ ማሳመር ነው። የቤት ኪራዩን ወጪም ሆነ የእለት ጉርሱን የሚያሟላው በዚሁ የሊስትሮ ስራ ነው፡፡
ወጣት ተሻለ ለትምህርት ያለው ፍላጎት ዛሬም አልተገታም፡፡ በችግር ምክንያት ያቋረጠውን ትምህርትም መቀጠል ይፈልጋል። ድጋፍ የሚያደርግለት አካል ካለም በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ስራ የመሰማራት ውጥኑ ዛሬም የእቅዱ አካል እንዳደረገ ነው የሚናገረው፡፡
ከሚሰራው የጫማ ማሳመር ስራ ከሚያገኛትም ቢሆን መቆጠብን ተለማምዷል። በቀን ከ150 እስከ 200 ብር ገቢ ያገኛል። ከወጪ ቀሪ ሲኖርም እንዳቅሙ ይቆጥባል፤ ከስራ ባልደረቦቹ ጋርም እቁብ ይጥል እንደነበር አስታውሶ አሁን ላይ ግን የኑሮ ውድነቱ ጫና እንደፈጠረበት ነው የሚናገረው፡፡
ለሌሎች አካል ጉዳተኞች አርዓያ ሆኖ የመታየት ህልም ያለው ወጣት ተሻለ ሀሳቡ እንዲሳካም ጥረት ማድረጉን አልተወም፡፡ ተስፋ ያለው እንጂ ተስፋ ቢስ ሆኖ መታየትን አይፈልግም፡፡ ተሻለ በስፖርቱም ዘርፍ በፓራኦሎምፒክ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን በአሎሎ ውርወራ ልምምድ እንደሚያደርግም ነው የተናገረው፡፡
አካል ጉዳተኞች በመሠረተ ልማት ችግር፣ ትምህርት፣ በሥራ እና በሌሎች የአካታችነት እጦት ሳቢያ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው ሲገደብ መመልከቱን ያነሳል።
ልዩ ችሎታቸውን ተጠቅመው ከራሳቸው አልፈው ሀገር እንዲጠቅሙ የማድረጉ ሥራም በክልል ደረጃ የተቀዛቀዘ እንደሆነ እንዲሁ። ስለዚህ ይህን የአመለካከት ችግር ከመሰረቱ በመቅረፍ አካል ጉዳተኞች በሁሉ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው