የይቅርታ ዜማዎች
በአንዱዓለም ሰለሞን
እነሆ አዲስ ዓመት ብለን ከጀመርነው 2017 ዓ.ም ወርሀ መስከረምን ሸኘን፡፡ ብዙዎቻችን፣ “መልካም ዜና የምንሰማበት፣ ሀገራችን ሠላም የምትሆንበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የደስታና የፍቅር ዓመት ያድርግልን…” በማለት የተመራረቅንበት መስከረም ቢያልፍም፣ ተስፋችን ግን አብሮን አለ፡-
ዘመኑን ጀመርነው ይኸው ታርቀን፡፡”
እንዲል ከያኒው፤ በይቅርታ ከዘመን ዘመን የተሸጋገሩ ምንኛ የታደሉ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው፤ “እንኳን ሰው እግርና እግርም ይጋጫል” እንዲሉ፣ ግጭት ያለ ነገር ነው፡፡ ሰው ከሰው ብቻም ሳይሆን ከራሱ ጋርም ይጋጫል። ከዚያም ሲያልፍ፣ ከፈጣሪው ጭምር። ነገሩን ከማህበረሰብ አንጻር ስንመለከተውም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ታወሰኝ መሰላችሁ፣ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ ያነበብኩት አንድ መጽሀፍ ላይ ያየሁት አንድ አባባል፡-
“ግጭትን በአግባቡ ማኔጅ (መቆጣጠር ለማለት) የሚያደርግ መሪ ካለ ግጭት በራሱ ለማህበረሰብ ዕድገት ጠቃሚ ነው፡፡ ግጭት ከራስ ይጀምራል፡፡ ከራስህ ጋር በቀን ሺህ ጊዜ ትጋጫለህ። ግጭትህን በአዎንታዊ መልኩ ካልተረጎምከው ራስህን ልትሰቅል ትችላለህ። …”
በመጽሀፉ ሌላኛው ገጽ ላይ ደግሞ፡-
“ብጥብጥና ግጭት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ግጭት ውስጥ ጥቅም አለ፡፡ ብጥብጥ የሚመጣው ግጭቱን በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻልክ ነው፡፡ …” ይላል፡፡
እዚህ ጋ የከያኒውን የዜማ ስንኞች ስናስከትል ደግሞ ነገሩ የበለጠ ትርጉም ይሰጣል፡-
“ስንኮራረፍ ጠላት ይስቃል፣
የአገርስ ነፋስ በማን ይደም ቃል?
ስማ ስጠራህ በዚህ ማሲንቆ፣
ይጥፋ ፀብ ሁሉ ሁሉም ሰው ታርቆ፡፡”
በእነኚህ ስንኞች የተቋጠረው ሀሳብ ጥልቅ ነው፡፡ ቢተነተን ብዙ አንቀጾች የሚወጡት ሀቅ እንዲህ በአራት መስመር ተገልጿልና፣ እንግዲህ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብዬ ልለፈው፡፡
የወጌ ርዕሰ ጉዳይ የሚያጠነጥነው፣ ይቅርታን የሚያጠይቁ የሙዚቃ ስንኞች ላይ በመሆኑ፣ ከማህበረሰብ ወደ ግለሰብ በመውረድ ነገሬን ልቀጥል፡፡ እዚህ ጋርም ታዲያ፣ ከአንድ ሙዚቃ ላይ ያገኘኋቸውን፣ ቀጣዮቹን ስንኞች ልጥቀስ፡-
“ኧረ አስታራቂስ የለም ወይ፣
ሀይ የሚለን ሰው ገላጋይ፤
ቀናት አለፉ ተኮራርፈን፣
ምን ነክቷችሁ ነው የሚል አጥተን፡፡”
ከማስታረቅ ጋር በተያያዘ የሚነሳና “ዋሽቶ ማስታረቅ” የሚባል ነገር አለ፡፡ በእርግጥ ከቃሉ አንጻር ሲታይ የውሸት ነገር ስላለበት አግባብ ያልሆነ ነገር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ግን ደግሞ፣ ለእርቅ ተብሎ የሚፈጠረው “ውሸት”፣ ነገሩን ለማዳፈን (ወቅት ጠብቆ እንዲፈነዳ) እና አለባብሶ ለማለፍ ሳይሆን፣ የተጣሉት ሰዎች ተቀራርበው እንዲነጋገሩ፣ በግልጽነት ተወያይተው እንዲተማመኑና ያጠፋውም ከልቡ ተጸጽቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ ለማድረግ ከሆነ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡
በተለይም በዘመናችን፣ ዋሽቶ የሚያጣላ መብዛቱን ከግምት ውስጥ ስናስገባ ደግሞ ጭራሽ መጥፎነቱ ላይታየንም ይችላል፡፡
ቀጣዮቹ የሙዚቃው ስንኞች የሚያስገነዝቡንም ይህንኑ እውነታ ነው፤ ፀብ ከማብረድና የተጣላን ከማስታረቅ ይልቅ፣ ነገር የሚያባብስ አቃጣሪ፣ “አክቲቪስት” መብዛቱን፡-
“ገላጋይ የለም አስታራቂ፣
አንተም አንቺም ተይ ’ሚል አዋቂ፤
እሳት የሚያበርድ የሚያጠፋ፣
አንድ የልብ ወዳጅ እንዴት ሸም ጋይ ይጥፋ፡፡”
እንግዲህ ይህን እውነታ የተረዳ ግለሰብ ሌላ ምን ይጠብቃል፤ ራሱ በቶሎ ይቅርታ መጠየቅ እንጂ፡፡ እርግጥ ነው፤ ጥፋቱ የእርሱ እንደሆነ የተረዳ ሰው፣ ይቅርታ ለመጠየቅ አስታራቂ እስኪመጣ መጠበቅ ስለምን አስፈለገው? እንል ይሆናል፡፡ ይህ እንግዲህ የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል” እንዲሉ፣ አንዳንድ “ጩኸታም” ሰዎች በድለው ይቅርታ መጠየቅ፣ ተበድለው ይቅርታ የማድረግ ያህል ይከብዳቸዋል፡፡ ይህም፡-
“ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ፣
ባሉባልታ አረስ ሀገር አደረሰ፡፡
የሚሉትን የአንዲት ድምፃዊት አንድ ሙዚቃ ስንኞች ያስታውሰናል፡፡ በደል የሰላም እንቅልፍ እንደማይሰጥ የተረዳና የይቅርታን ታላቅነት የተገነዘበ ሰው ግን፣ ለሁለቱም (ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ይቅር ለማለት) አይሰንፍም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሸምጋይ አያስፈልገውም፡-
“ሁሉን ነገር ትቼ ይቅርታ ልጠይቅ
አስታራቂም የለን እኛው እንታረቅ”
እንዲል ከያኒው፡፡
ይህንኑ ሀሳብ የያዙ ስንኞችን፣ በሌላ ድምጻዊት አንድ ሙዚቃ ላይም እናገኛለን፡-
“ፍቅር ባያዛልቅ ኩርፊያ ይበጃል ወይ፣
የበደለ ክሶ አንታረቅም ወይ፤
ጨክኜ ላልተውህ ቆርጠህ ላትተወኝ፣
ይቅር እንባባል ልለፍህ እለፈኝ፡፡”
ዝምታው ጥፋትን ባለማመን አልያም በሌላ አሉታዊ ነገር ሳይቆጠር፣ ጊዜ ሳይወስዱ እንዲህ ይቅርታ መጠየቁ መልካም ነው። አልያ ግን፣ ተኳርፎ መክረሙ ሲቀጥል፣ ነገሩ መልኩን ቀይሮና ተካሮ ለእርቅ ሊቸግር ይችላል፡፡ ቀጣዮቹ የሌላ ድምጻዊ አንድ ሙዚቃ ላይ ያሉ ስንኞች የሚያስገነዝቡንም ይህንኑ እውነታ ነው፡-
“የሰራሽኝ በደል ስሩ ከሰደደ፣
ይቅርታሽ ደረሰኝ ምነው ከረፈደ፤
ለይቅርታው ጊዜ አልዘገየሽም ወይ፣
ያፈቀረ ጊዜው አይረዝምበትም ወይ።”
ይቅርታ በፈጣሪ ዘንድም የተወደደ ነገር ነው፡፡ መንፈስን የሚያድስ፣ ልብን ከቂም በቀል የሚያነጻ። ለዚህ ደግሞ፣ ይቅርታ ጠያቂው ሁኔታውን የሚገልጸው ከልብ በመነጨ ስሜት ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር፣ እነዚህ የሌላ ድምጻዊ አንድ ሙዚቃ ላይ ያሉ ስንኞች የሚነግሩን ነገር ይኖራል፡-
“ተንገበገበልሽ አረረልሽ ሆዴ፣
አትራቂኝ በኔ ሞት አይብዛ መንደዴ፣
ያስታርቀን መውደዴ፤
ልመናዬን ስሚ ይቅርታሽ ይድረሰኝ፣
ጥፋቴን ለመርሳት እኔ አቅም አነሰኝ፣
ልቤ እየወቀሰኝ፡፡”
በጸጸት የተሞላው ልመና ጥፋትን በማመን እንዲህ ገሀድ ሲወጣ፣ ይቅርታ ጠያቂው የተማመነበትና ያስታርቀናል ብሎ ያመነበት ነገር ሁለቱን በጠረጴዛ ዙሪያ የሚያደራድር ግለሰብን አይደለም፡፡ “ያስታርቀን መውደዴ” የሚለው ስንኝ እንደሚነግረን፣ ለእርቅ ተስፋ ያደረገው ለእሷ ያለውን ፍቅር ነው፡፡ “ፍቅር በደልን አይቆጥርም” ይባል የለ፣ ይህ ደግሞ ከበደላት ግለሰብ (ፍቅረኛው) አዎንታዊ ምላሽን ያገኝ ዘንድ ከምንም በላይ ዋስትና የሚሆነው ነገር መሆኑን አምኗል፡፡
ነገሩን ከዚህ አንጻር ካየነው ዘንዳ፣ በእሷ በኩል ምላሿ ምን ሊሆን ይችላል? ብለን ብንል፣ በሁለቱ ልብ ውስጥ ከነበረው ጥልቅ ስሜትና ከፍቅር ሀያልነት አንጻር መልካም የመሆኑ ዕድል ሰፊ ነው ብለን ማሰብ እንችላለን፤ ምናልባትም በዚህ ቀጣዩ የአንዲት ድምጻዊት የሙዚቃ ስንኞች የሚገለጽ ዓይነት፡-
“ይቅር ብዬሀለሁ ለጥፋትህ፣
ደጉን ቀን አስቤ ትቼ ክፋትህን፤
ቢከፋም በደልህ በእኔ የሰራኸው፣
ልቤን ቢያደማውም ይቅር ብያለሁ፡፡”
እንዲህ ባለ መልኩ ይቅርታ ማድረግና በደልን መርሳት፣ ታላቅ አስተዋይነትን ብቻም ሳይሆን ቀና ልቦናን የሚጠይቅ ጭምር ነው፤ ከጀግንነት የሚቆጠር፡፡ ቀጣዮቹ የሙዚቃው ስንኞች ደግሞ የነገሩን ከባድነት ያስረግጡልናል፡-
“አስቀይመኸኝ ልቤን ብትጎዳው፣
እየዋሸኸኝ ሆዴን ቢከፋው፣
ማለት ይሻላል ይቅር ብያለሁ፡፡”
ከበደሉ ክብደት አኳያ፣ ያለፈውን በመርሳትና ይቅርታ በማድረግ ውስጥ ታዲያ፣ ወደ ቀድሞው ነገር ለመመለስ መቸገርም ሊስተዋል ይችላል። እዚህ ላይ፣ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ይቅርታነቱ? የሚል ካለ፣ ይቅርታውማ ልብን ከቂም በቀል ከማንጻት አንጻር ነው፣ ይሆናል ምላሹ፡፡ ልብ ዳግም እንዳይደማ ሲባል የትናንቱን ህይወት “ቀይ መስመር” የሚያሰምሩበት፣ “የተገደበ” ይቅርታ እንበለው ይሆን? ቀጣዮቹ የሙዚቃው ስንኞች ይህ ዓይነቱ የስሜት ነፀብራቅ የሚስተዋልባቸው ናቸው፡-
“ያለፈን ትቼ ’ላሁን ባስብም፣
ሠላም አስቤ ፍቅርን ብወድም፣
ፍቅሬን ዳግመኛ ላንተስ አልሰጥም፣
ይቅር ብያለሁ ይቅርታ አይከብድም፡፡”
እንግዲህ ይቅርታ እንዲህም ሊሆን ወይም በዚህ መልኩ ሊገለጽም ይችላል ማለት ነው፤ አንድም ስላሳለፉት መልካም ጊዜና ፍቅር ሲሉ፣ ሁለትም ዳግም ላለመጎዳት በማሰብ፣ በደልንም ፍቅርንም ይቅር ብለው፣ በፍቅርና በይቅርታ የሚያልፉበት!
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው