በመሐሪ አድው
የዛሬው እቱ መለኛችን የልጅነት ምኞታቸው የነበረው ኢንጂነር መሆን ነበር። የትምህርት አቀባበላቸውም ህልማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ነበር፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ የደረጃ ተማሪ ሆነው ነበር የዘለቁት። ሆኖም ግን የቤተሠባቸው አቅም ውስንነት ከህልማቸው ጋር የሚያገናኛቸው ሆኖ አልተገኘም፡፡
የቤተሠባቸው የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ ቢሆንም በልጅ አስተዳደግ፣ በሥነ-ምግባርና ስብዕና ግንባታ ረገድ እጅግ የበለፀጉ በመሆናቸው ልጆቻቸውን በመልካም አስተዳደግ መቅረፁ የተሳካላቸው ናቸው። እቱ መለኛችንን ለዛሬ ማንነት ያበቃቸው ይሄው አስተዳደግ ነው፡፡
ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ ወልዱ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቡር ዞን መቱ ከተማ ነው፡፡ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት በተወለዱበት አካባቢ ነው፡፡
ትምህርታቸውን ሲማሩ ምንም እንኳን ጐበዝ ተማሪ የሚባሉ ቢሆኑም ራስን በራስ እየረዱ መማር አዳጋች ሆኖባቸው ነበር። የመማር ፍላጐቱና ጉብዝናው ቢኖርም የኢኮኖሚ አቅሙ በቂ ባለመሆኑ ከ1ዐኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ፡፡
በዚህም ገፊ ምክንያት በ1979 ዓ.ም የማረሚያ ፖሊስ አባልነትን ተቀላቀሉ። በፖሊስ ማሠልጠኛ ተቋምም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ አውግተውናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በልጅነታቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሠንበት ትምህርት ቤት በዝማሬ ያገለገሉ በመሆናቸው በፖሊስ ቤትም በኪነት ውስጥ የጐላ ሚና ነበራቸው፡፡
በፖሊስ አባልነትም እያገለገሉ ትዳር የመሠረቱት ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ፣ ሦስት ወንዶች ልጆችን ማፍራት ችለዋል፡፡
ቤተሠብ ማስተዳደርንና ህዝባዊ ሃላፊነትን አጣምረው የያዙት እኚህ ጠንካራ ሴት ፈተናዎችን ሁሉ እየተጋፈጡና እየተሻገሩ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በተገቢው ተወጥተዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት የቤት እመቤትነትና ፖሊስነት ሁለቱ አንድ ላይ ለሴት ልጅ ከባድ ሊሆን ይችላል ካከበዱት፡፡ ቀለል አድርገው ካዩት ግን ብዙ ነገር መሥራት እንደሚቻል ከእኔ ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል ባይ ናቸው፡፡
የእንቅልፍ ሠዓታቸውን ቀንሰው ነው በልጆቻቸውም በሥራቸውም በኩል ክፍተት እንዳይፈጠር አቻችለው የሚሄዱት፡፡
ረዳት ኮሚሽነሯ ሥራቸውን ሲሰሩና ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ስልጣንና የማዕረግ እድገት አገኛለሁ የሚለውን አስበው አይደለም፡፡ ሃላፊነታቸውን ሲወጡም በውስጣቸው ከማንም አላንስም የሚል ፅኑ እምነት ስለነበራቸው ብቻ ነው በስራቸው ስኬታማ መሆን የቻሉት፡፡
መደበኛ የፖሊስ አባል ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ያስመዘገቡ በመሆናቸው ከ2ዐዐ3 ዓ.ም ጀምሮ የኢሉባቡር ዞን ማረሚያ ቤት ዋና ሃላፊ ሆነው ነው ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ እያገለገሉ የሚገኙት፡፡
በማረሚያ ቤት ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸውንና በቁጥራቸው ልክ የተለያየ ባህርይ ያላቸውን ታራሚዎችን ነው የሚያስተዳድሩት፡፡ የማረሚያ ፖሊስ አባላትም ከ15ዐ በላይ መሆናቸውን ረዳት ኮሚሽነሯ ነግረውናል፡፡
በታራሚዎችም ይሁን በአባላቱ ውስጥ ያለው የተለያየ ባህርይን አርቆ መምራት ለሴት ልጅ በጣም ከባድ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን ሃላፊነት ከበቂ በላይ እንደሚወጡት ማስመስከር የቻሉ ናቸው፡፡
በየደረጃው ያሉ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎችንና አባላትን፣ እንዲሁም ታራሚዎችን በማስተባበር የተለያዩ የልማት ትሩፋቶች እንዲገኙ አድርገዋል፡፡
በአብዛኛው ሠው ዘንድ ማረሚያ ቤቶች የሲኦል ተምሳሌት ተደርገው ነው የሚወሰዱት። ይህን አመለካከት መቀየር አለብን የሚል አቋም የያዙት ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ ወልዱ፣ የኢሉባቡር ማረሚያ ቤትን በተለየ ሁኔታ ወደ መናፈሻነት መቀየር መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
ቀደም ሲል በቆሎ ብቻ ይዘራበት የነበረውን ማረሚያ ቤት ወደ ሌላ ልማት ለማስገባት ባደረጉት ጥረት የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን በብዛት እንዲተከል አደረጉ፡፡ ህብረተሰቡ እነዚህን ለመግዛት በሚል ወደ ማረሚያ ቤቱ በመምጣት እንዲቀራረብ አደረጉ፡፡
በቀጣይ መዝናኛው ሊሠራ ሲታሰብ ወደ መዝናኛው ሠው ሲመጣ የታራሚዎችንና የአባላቱን ድካምና ጥረት መገንዘብ ጀመረ፡፡ የመጡ ለውጦችንም ተመለከተ፡፡
የኢሉባቡር ዞን በተፈጥሮ ፀጋና በደን የበለፀገ ቢሆንም የህዝብ መናፈሻና መዝናኛ ግን የለውም ነበር፡፡
ይህን የተገነዘቡት ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ ማረሚያ ቤቱ ከነበረው 54 ሄክታር መሬት 11 ነጥብ 25 ሄክታር ቦታ ላይ የመዝናኛ ቦታ ያሠሩ ሲሆን በዚያ ውስጥ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ሠው ሠራሽ ሃይቅ ተሠርቶበታል። በሃይቁ ውስጥ ደግሞ የዓሣ እርባታ የሚሠራበት ሲሆን የጀልባ አገልግሎትም ይሠጣል፡፡
የተወሰኑ አዳራሾችም ተሠርተዋል። የአካባቢውን ባህል የሚያንፀባርቁና በገዳ ሥርዐት የተሠሩ “ሳልገል ኢሉ” የሚባሉ ጐጆ ቤቶችም አሉት፡፡ በመናፈሻው እዚያው የተመረቱ አትክልትና ፍራፍሬዎችም በጭማቂና ቁርሳ ቁርስ መልኩ ይሸጣሉ፡፡
በመናፈሻው የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎችን በመትከል በአረንጓዴ የተሸፈነ እጅግ ሳቢና ውብ በማድረግ ለህብረተሠቡ የመዝናኛ አማራጭ መፍጠር ችለዋል፡፡ ስለዚሁ ሁኔታ ረዳት ኮሚሽነሯ ሲያብራሩ፡-
“በአምስት ሄክታር መሬት ላይ ቡና፣ በአምስት ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ የሻይ ቅጠል ተክለናል፡፡ በስድስት ሄክታር መሬት ላይም ደኖችን በመትከል ለማረሚያ ቤቱ ተጨማሪ ገቢ ማመንጨት የሚችል ተግባር ፈፅመናል፡፡ በዚህም በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ምርት ማምረት የሚቻልበት ማድረግ ችለናል፡፡” ብለዋል፡፡
ታራሚውን ከማረምና ከማነፅ ባሻገር በልማት ሥራ ማሳተፍም የማረሚያ ቤቱ አብይ ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑት ታዲያ ከመንግስት በጀት ላይ ሳይሆን በራስ ተነሳሽነት ባመነጩት የውስጥ ገቢ ነው፡፡
ረዳት ኮሚሽነሯ እንደነገሩን መንግስት እገዛ ያደረገላቸው አብዛኛው የፓርኩ ሥራ ከተገባደደ በኋላ ለመዋኛ ገንዳ ማሠሪያ የሚሆን ብር ብቻ ነው፡፡ ሌላው የተሠራው አስተዳደሩ፣ አባላቱና ታራሚዎች ተናበው በፈጠሩት ህብረት ነው፡፡
የመዝናኛ ተገልጋይ የአካባቢው ማህበረሠብ ሲሆን ለሠርግና ለተለያዩ ግብዣዎች ይጠቀሙበታል፡፡ መዝናኛው በአንድ ጊዜ ከሃያ በላይ ሠርጐችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ ከፍተኛው ክፍያ 1 ሺህ 500 ብር ሲሆን ለኮቴ የሚከፈለው አሥር ብር ነው፡፡
አባሎች የወር ደመወዛቸው አነስተኛ ስለሆነ የሚገጥማቸውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ታስቦ ወደ ስድሳ ሠዎች ለሚሆኑ መኖሪያ ቤት በማረሚያ ተቋም ውስጥ በመስራት እዚያው እንዲኖሩ ማድረግ ችለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በማረሚያ ቤቱ ዙሪያ ትናንሽ ሱቆችና የንግድ ቤቶችን በመክፈት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሠቡ ቁሳቁስ በማቅረብም የህዝቡን የኑሮ ውድነት ለማቅለል ጥረት እንደሚደረግ ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ ነግረውናል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ባለው ትርፍ ቦታ ላይ ትላልቅ አዳራሾችን፣ ሎጆችንና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መስራት ቀጣይ እቅዳቸው መሆኑን የኢሉባቡር ዞን ማረሚያ ቤት ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ተናኘ ወልዱ አጫውተውናል። ማረሚያ ቤቱ በሀገሪቱ ላሉት ማረሚያ ቤቶች መልካም አርአያ ስለመሆኑም በተለያዩ መድረኮች ተደጋግሞ እንደሚነሳም አክለው ተናግረዋል፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ