ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመንገድ ደህንነት፣ በአደጋዎችና በመፍትሔዎች ዙሪያ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለሚገኙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በቦንጋ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።
የስልጠናውን መድረክ በንግግር የከፈቱት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሚዲያ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ በረከት ኢዮብ፤ ሚዲያ በትራፊክና በመንገድ ደህንነት ዘርፍ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 69 ሞት እና 219 የአካል ጉዳት መመዝገቡን የጠቀሱት ወይዘሮ በረከት፤ ከ24 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ተናግረዋል።
ኃላፊነታቸውን በሚዘነጉ አንዳንድ አሽከርካሪዎች የሚስተዋሉ ትርፍ መጫን፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከርና ደንብ መተላለፎች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የመኪና አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት ወደ 1.2 ሚሊየን የሚጠጋ የሰው ሕይወት የሚነጥቅና ከ50 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የአካል ጉዳት መንስኤ መሆኑን የተናገሩት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ምርምር ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን ናቸው።
ኢትዮጵያ ያላት የመኪና ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በርካታ ተሽከርካሪ ካላቸውና የመንገድ መሠረተ-ልማት ከተሟላላቸው ሀገራት አንጻር ከፍተኛ የመኪና አደጋ ጉዳት የሚከሰትባት ሀገር በመሆኗ ዘርፉ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።
ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 29 ያሉ ህጻናትና ወጣቶች ከፍተኛ ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ጌታቸው፤ ይህም ከአጠቃላይ አደጋ 59 ከመቶ ያህሉን የሚሸፍን ነው ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ነጋ ጅባት፤ አንድም ሰው በመኪና አደጋ መሞት የለበትም የሚል ግብ አስቀምጠው የሚሰሩ ሀገራት የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያም ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ማስተካከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የፍጥነት ወሰን አለመጠበቅ፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ አለመጠቀም፣ ትኩረት የሚያስቱ ሁኔታዎች ውስጥ መሆንና የተለያዩ እፆችን መጠቀም ለአደጋ መፈጠር ዋነኛ መንስኤዎች እንደሆኑ አመላክተዋል።
ቀበቶና የህጻናት ደህንነት መጠበቂያን በአግባቡ መጠቀም ከ70 እስከ 80 በመቶ የአደጋ ጉዳትን የመቀነስ እድል እንዳለው መክረዋል።
ካነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሚዛን ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ ፍቅማሪያም ዳኜ እና በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ሬዲዮ ጣቢያ ሪፖርተር ዳንኤል መኩሪያ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ለሥራቸው ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመንገድ ደህንነት ችግር በዜጎችና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እውቀት ላይ የተመሰረቱ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ሰፊ የግንዛቤ ሥራ በማከናወን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ለተግባራዊነቱም ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ መተባበር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የኑሮ ጫናን ለመቀነስ አጋዥ መሆናቸውን የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ገለፀ
ወጣቱ በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ በመሆን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ እንዲያመጣ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ከጠልቃ ገብነት፣ ከዕንግልትና ገንዘብ ብክነት በፀዳ መልኩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ