እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በከተማው በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሠራ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ በማሳለጥ ከተማዋን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለሆሳዕና ጣቢያችን አስተያየታቸውን ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አየለ አሼቦ፣ ሚልክያስ ሳየቦ እና በተላ በቀለ እንደገለጹት፤ በሀገራችን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሰብ አመንጪነት በተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ በከተሞች እየታየ ያለው ለውጥ የሚበረታታ ነው።
በሙዱላ ከተማም ይህ ስራ መጀመሩ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብናል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ እየተከናወነ ያለውን የኮርደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በሙዱላ ከተማ እተከናወነ ባለው የኮርደር ልማት ሥራ በጉልበት፣ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሀብት በማሰባሰብ እንዲሁም በሙያቸው በመታገዝ ሥራው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰራ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የገለፁት ወጣት አማኑኤል አለማየሁ፣ አንለይ አሰፋ እና ወንዶሰን ወ/ሚካኤል ሥራው እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የሙዱላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እሼቱ ሙላቱ እንደተናገሩት፤ በከተማው የህብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከተማው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
በዘንድሮው ዓመትም ከከተማ አስተዳደርና ከልዩ ወረዳው ጋር በመነጋገር በከተማው ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ በርካታ ከሀገር ውጭ እና በአገር ውስጥ የሚኖሩ የጠምባሮ ተወለጆችና ወዳጆች የተሳተፉበትና በህብረተሰቡም ዘንድ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር በሁለት ሳይት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አሁን በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ቀጣይ በሦስት ሳይቶች የኮሪደር ልማት ሥራውን ለማስቀጠል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ እሼቱ፤ ህብረተሰቡ ከተማውን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በሚሰሩ ሥራዎች የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደስታ ዶባሞ በበኩላቸው፤ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሥራዎችን በማከናወን በ2017 ዓ.ም በክልሉ ከሚገኙ ፈርጅ 3 ከተሞች የሙዱላ ከተማ የመጀመሪያውን ደረጃ በመያዝ በክልል ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ12 ሚልዮን ብር ባላይ የገንዘብ ወጪ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ሥራ የሀብት ማሰባሰብ ሥራውን የመከታተልና የመደገፍ ሥራዎች እንደሚቀጥሉም ከንቲባው ጠቁመዋል።
ከንቲባው አክለውም፤ ከሀገር ውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ የአካባቢው ተወላጆችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች አቅማቸው በፈቀደ ልክ ስራው እስኪጠናቀቅ የድርሻውን ሊወጡ አንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ
ከ2 ሺህ በላይ አዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መታቀዱን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቃ