ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ
የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ለትምህርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡን አሳትፎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።
በወረዳው ቆንጋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተን ካነጋገርናቸዉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ኤልያስ ብርሃኑ እና ትዕማር አሸናፊ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በክፍልና ከክፍል ውጪ የሚሰጡ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመስራት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ተማሪ ፍሬነሽ መንግስቱና መልካሙ ጎበና በወረዳው የቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ በትምህርት ቤታቸው የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት መኖሩን ጠቁመው የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት በመስጠት ችግሩን እንዲቀርፉላቸው ጠይቀዋል።
አቶ ገደቾ ጀቦ በወረዳው የቆቄ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የመማሪያና የማስተማሪያ መጻሕፍት እጥረት በመንግስት በጀት ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑ ገንዘብ እያዋጡ እንደሆነ ገልጸው ሁሉም የቀበሌው ነዋሪዎች ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
መምህርት ፀጋነሽ ማሞ እና መምህር አበራ ጠቀቦ በቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪዎች ሲሆኑ ከመማሪያ መጻሕፍት ባለፈ የማስተማሪያም እጥረት መኖሩን ጠቁመው በተፈለገው ልክ ለማስተማር ማነቆ እንደሆነባቸው ነው የተናገሩት።
በወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የሥርዓተ ትምህርትና የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦት ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ፈቃዱ በየነ፣ በወረዳው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች በአማካይ አንድ መጽሐፍ ለሶስት እንዲሁም ከ9ኛ እሰከ 12ኛ አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ መዳረሱን ተናግረዋል።
በወረዳው በተወሰነ መልኩ የሒሳብ፣ የአካባቢ ሣይንስ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መጻሕፍት እጥረት መኖሩን ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት ለዞን ትምህርት መምሪያ በማሳወቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ጠገኖ፣ በወረዳው 45 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ የ2018 የትምህርት ሥራ በተጀመረ ማግስት ለትምህርት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል የመማሪያና የማስተማሪያ መጻሕፍት በተወሰነ መልኩ ለተማሪዎችና ለመምህራን እንዲደርሱ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የግብዓት አቅርቦትን ለማሳለጥ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ባለሀብቶችን እና ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
መንግስት በርካታ በጀት አፍስሶ ያሳተማቸውንና አሁን ላይ በተማሪዎችና በመምህራን እጅ የሚገኙ መጻሕፍትን በንጽሕና በመያዝ በኃላፊነት ስሜት እንዲገለገሉባቸውም አቶ ፍቅሩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ
                
                                        
                                        
                                        
                                        
More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ከ2 ሺህ በላይ አዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መታቀዱን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቃ