“ከቆቦ ዛፍ የተሽከርካሪ ነዳጅን መፍጠር የቻለው” – ወጣት ታሪኩ አዳነ

“ከቆቦ ዛፍ የተሽከርካሪ ነዳጅን መፍጠር የቻለው” – ወጣት ታሪኩ አዳነ

የትኛውም የፈጠራ ስራ የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ ሊሆን እንደሚገባ በኢትዮጵያ 2016 የ”ብሩህ ኢትዮጵያ” የፈጠራ ስራ ውድድር አሸናፊ መምህር ታሪኩ አዳነ ይናገራል።

ወጣቱ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከቆቦ ዛፍ የተሽከርካሪ ነዳጅን በመፍጠር ነው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ አሸናፊ የሆነው።

በሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአውቶሞቲቭ መምህር ሆኖ ያገለግላል፡፡ ታሪኩ አዳነ ከልጅነቱ ጀምሮ ህልሙ እንደነበረ የሚናገረውን የፈጠራ ስራ፤ በ2016 የብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ ይዞ በመቅረብ በሀገር አቀፍ ደረጃ አሽናፊ ሆኗል።

ወጣቱን መምህር ለአሸናፊነት ያበቃው ከቆቦ ዛፍ የፈጠረው የተሽከርካሪ ነዳጅ ሲሆን በዚህም የዕውቅና ሠርትፍኬትና የ2 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ መሆን ችሏል።

የፈጠራ በለሙያው ወጣቱ ከደሬቴድ ሆሳዕና ቅርንጫፍ ጋር ባደረገው ቆይታ “የትኛውም የፈጠራ ስራ የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ ሊሆን ይገባል ብሏል።

በአለማችን የዕለት-ተዕለት ጥያቄ እየሆነ የመጣው የነዳጅ አቅርቦት ችግር በሀገራችን ላይም እያስከተለ ያለውን የኢኮኖሚ ጫናን በመረዳት ወደ ፈጠራ ስራ መግባቱን የሚናገረው ታሪኩ፤ ምርቱ ወደ ትግበራ ሲገባ የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚቀርፍ ከመሆኑም ባሻገር ከብክለት የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነ ነው የገለፀው።

ምርቱም ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ግብዓትና ባለሙያ የሚመረት በመሆኑ ካልተገባ ኪሳራና የኃይል ብክነት በመታደግ የዜጎች ሕይወት በኢኮኖሚውም ሆና በጤና ጫና ውስጥ ሳይገባ መኖር እንዲችል ያግዛል ነው ያለው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለውድድር ይዞ ከቀረበው የፈጠራ ስራ በተጨማሪ ሌሎችም ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች በእጁ እንደሚገኙ በመግለፅ ከሀዲያ ዞን ባለድርሻ ተቋማትና ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገረው።

ለነዳጅ ፈጠራ የቆቦ ዛፍ ፍሬ መጠቀሙን በመግለፅ ለአርሶ አደሩ ይህንን ተክል የማስፋፋት ልምድ ማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚያስገኝ እንደሆነም አስረድቷል።

ጊዜው በቴክኖሎጂ የተደገፋ መሆኑ በፈጠራ ስራችን ይበልጥ ውጤታማ የምንሆንበትን ዕድል ይዞልን የመጣ ነው የሚለው የፈጠራ በለሙያው የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ይህንኑ ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙበትም አመላክቷል።

የፈጠራ ስራ በባህሪው በተግዳሮቶች የተሞላ እንደሆነ በመግለፅ በሁኔታዎች ተስፋ ሳይቆርጡ አዘወትሮ መሞከርን ልማድ ማድረግ ለአሸናፊነት እንደሚያበቃም አንስቷል።

የፈጠራ ሃሳብና እንቅስቃሴ ያላቸውን ወጣቶች ለመደገፍና የግሉን ተሞክሮ በፈቃደኝነት ለማጋራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህም ፍላጎቱ ላላቸውና ለፈጠራ ስራ ህልመኞች መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ብሏል።

ወጣቱ በሌላ የፈጠራ ስራ ከህንድ ሀገር ተሞክሮ በመውሰድ በሆሳዕና ከተማ በአመት የሚወጣውን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻን መልሶ በጥቅም ላይ ለማዋል ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ እንደሚገኝና ለኮሌጁ በተለይ በሰራው የፈጠራ ስራ የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚ መሆኑንም ተናግሯል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ያደረገው የተሽከርካሪ የነዳጅ ፈጣራ ስራ በቀጣይ ከሀገር ውጪ በዱባይ አቡዳቢ ለውድድር እንደሚቀርብ ጠቁሞ ለዚህም ከወዲሁ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝና በዉድድርም አሸንፈው ሀገርን የማስጠራት ህልም እንዳለውም ጨምሮ ገልጿል።

በመጨረሻም ወጣቱ ለዚህ ስኬት እንዲበቃ ከሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጀምሮ በልዩ ልዩ ድጋፎች ከጎኑ ለነበሩ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል።

አዘጋጅ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን