ግብጽ የማያዋጣትን መርጣለች

ግብጽ የማያዋጣትን መርጣለች

በኢያሱ ታዴዎስ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የወራት ብቻ ዕድሜ በቀራት ሰዓት አሁንም በግብጽ በኩል ውዝግብ አልጠፋውም፡፡ ግብጽ ግድቡ የመጠናቀቂያ ምዕራፉ ላይ ሳለ ጉንተላዋን አለማቆሟ ትዝብት ውስጥ ጥሏታል፡፡

የግብጽ አካሄድ ጂኦፖለቲካዊ መልክ ተላብሶ ቀጣናውን ወደ ማመስ ተሸጋግሯል፡፡ የሕልውና ስጋት ተጋርጦባት ምትይዝ ምትጨብጠውን ያጣችውን ሶማሊያን ወዳጅ አድርጋ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ሁነኛ መሳሪያዋ ካደረገች ዋል አደር ብላለች፡፡

የራሷ ፖለቲካ ያረረባት ሶማሊያ የአልሻባብን ጥቃት ማስታገስ አቅቷት በምትማስንበት በዚህ ጊዜ፣ ከግብጽና ጀሌዎቿ ጋር የፈጸመችው ጊዜያዊ ጋብቻ ወዴትም እንደማያራምዳት ሳይጠፋት አልቀረም፡፡

ግብጽን ተመክታ የዘመናት ወዳጇን ኢትዮጵያ በክህደት ለመውጋት መነሳቷ የእውር ድንብር አካሄድ ስለመምረጧ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አሁን ድረስ ይፋ እንደሚያደርጉት ግብጽ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ሶማሊያ ማጋዟን ቀጥላበታለች፡፡

ግብጽ በባለፈው የፈረንጆቹ ነሐሴ ወር በጋራ የጦር ልምምድ ለማድረግ የሚያስችል የጦር መሳሪያ ድጋፍ ካደረገች ወዲህ በቅርቡ ዳግም በመርከብ አስጭና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን መዳረሻቸውን ሞቃዲሾ ላይ አድርጋለች፡፡ ግብጽ ይህንን እርዳታዋን የሶማሊያን ሕልውናና ደህንነት ማስጠበቅ የሚል ሽፋን ሰጥታው ነው እየተንቀሳቀሰች ያለው፡፡

የጦር መሳሪያዎችን ወደ ሞቃዲሾ የማጋዝ ተልዕኮ ሰሙም ሆነ ወርቁ የተደበቀ አይደለም፡፡ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ማስቆም ባለመቻሏ የበቀል እርምጃ መውሰጃ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ውጥረት ለመፍጠር ያስችላት ዘንድ እንቅስቃሴዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡

ነገሮች ግን ግብጽን ለተማመነችው ሶማሊያ እንዳሰበችው ቀላል አልሆኑላትም፡፡ የአልሻባብን አከርካሪ በመስበር የሚታወቀው የኢትዮጵያ ወታደር ኃይል እግሩን ከሞቃዲሾ አነሳ ማለት የሀገሪቱ ሕልውና አስጊ ደረጃ ደረሰ ማለት ነው፡፡

በባለፈው የፈረንጆቹ ነሐሴ ወር መጀመሪያ በሞቃዲሾ ባህር ዳርቻ ላይ አንድ ግለሰብ አጥፍቶ የማጥፋት አደጋ ካደረሰ በኋላ ሌሎች ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ 32 ንጹሃን ዜጎች ለሕልፈት፣ ከ60 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

ተመሳሳይ ጥፋት የማያጣት ሶማሊያ ከሰሞኑም አልሻባብ ባደረሰው የቦምብ ጥቃት ከ12 በላይ ሰዎችን ለሕልፈት፣ እንዲሁም በርካቶችን ለቁስለት የዳረገ ጥቃት ተፍጽሞባታል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም ባለፉት 2 ወራት ብቻ አልሻባብ በሞቃዲሾ 11 የተለያዩ ጥቃቶችን ፈጽሞ ለ200 ንጹሃን ዜጎች ሞት ተጠያቂ ሆኗል፡፡

ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል አልሻባብን በማስተንፈሱ ረገድ የሚጫወተውን ሚና ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ሶማሊያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ብዙ መስዋዕትነትንም ከፍሏል፡፡

አሁንም ቢሆን የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ አካል በመሆን ኢትዮጵያ በቋሚነት ወታደሮችን በሀገሪቱ እንዳሰፈረች ይነገራል፡፡

ታዲያ በዚህን ያህል ደረጃ ለሶማሊያ ሕልውና ትርጉም ያለውን የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል፣ ሶማሊያ እስከ ፈረንጆቹ 2024 ማብቂያ ድረስ ሙሉ ለሙሉ ከግዛቴ ይውጣ ማለቷ በራሱ የሚጣረስ ነው፡፡

አልሻባብን መመከት አቅቷት ራስ ምታቷን ማስታመም ባልቻለችበት ሁኔታ፣ የግብጽን ሆይ ባይነት ብቻ ሰምታ ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዳር ዳር ማለቷ የጉድ ሀገር አስብሏታል፡፡ ቀጣይ እርምጃዎቿ ከኢትዮጵያ ጋር የሻከረውን ግንኙነት የሚያለሰልስ ካልሆነ የከፋ ጉዳት እንደሚጠብቃት መገመት የዋህ አያስብልም፡፡

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ዓላማዋ ግጭት ውስጥ መግባት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ በመሪዎቿ በኩል ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ ሶማሊያ ጥርስ የነከሰችበት ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የባህር ወደብ ስምምነት ቀጥተኛ ተጎጂ እንደማያደርጋት ደጋግማ ስታሳስብ ቆይታለች፤ የሶማሊላንድ ራስገዝነት ጉዳይም ቢሆን ያለቀለት እንደሆነ ታምናለች፡፡

ሶማሊያ አልሻባብ እንደዚያ የቦምብ ዶፍ እያዘነበ ቁም ስቅሏን ሲያሳያት ግብጽ አንድም ከለላ ለመሆን ያደረገችው ጥረት አልነበረም፡፡ ዛሬ ደርሶ ሰላም አስከባሪ ለመምሰል ወታደሮቼን ልኬ አሳርፍሻለሁ ማለቷ የይምሰል እንጂ ካንጀቷ እንዳልሆነ የግብጽን ስነልቦና የተረዳ ሁሉ ያውቀዋል፡፡

የግብጽ ዓላማ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ግብፅ ለየትኛውም ሀገር ሰላምና ደህንነት ስትል ሰርታ አታውቅም፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑትን ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ኬኒያ ወደ ማባበል የገባችው፡፡ አሁን አሁን እነዚህን ሀገራት ከእኔ ወዲያ ወዳጅ የላችሁም ለማለት በሚመስል ሽርክናዋን አጠናክራለች፡፡

ይህ ሁሉ ዳር ዳርታ ቀን ሲከፋ ጠብቃ ኢትዮጵያን ከእስከአሁኑ የስውር ጥቃቷ በዘለለ ደግሞ በገሃዱ ፈጦ የታየ ነው፡፡ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቋጠረችውን ቂም በጦርነት ማወጣት ትፈልጋለች፡፡ ለዚሁ ዓላማዋ ደግሞ መሳሪያ ያደረገችው የኢትዮጵያን ጎረቤቶች ነው፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ በታሪኳም ቢሆን የሀገራት ሉኣላዊነትን ተጋፍታ አታውቅም። ለዚህም ለዘመናት የዘለቀው ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶቿ ምስክሮች ናቸው፡፡ አሁን አሁን በግብጽ ግፊት ሀገራት ጀርባቸውን ሊሰጧት ቢዳዱም ዲፕሎማሲያዊ አካሄዱን ታውቅበታለችና የማለሳለስን ጥበብ መጠቀሙን መርጣለች፡፡

ጎረቤቶቿን በወዳጅነት መያዟንም ቀጥላበታለች፡፡ ኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ለዚሁ ማሳያ ናቸው፡፡ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያኮረፈችው ሱዳን የገጠማትን የውስጥ ቀውስ ለማርገብ፣ ኢትዮጵያ ድጋፏን ታደርግ ዘንድ በሮቿን ከፍታ እንደምትጠብቅ በተደጋጋሚ ማስታወቋ የኢትዮጵያን ቀናነት ያሳብቃል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ እንደጎዳቻት በዓለም አደባባይ ጩኸቷን እንዳሰማችው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ግብጽ ወደ ጦርነት እየተንደረደረች ስለመሆኗ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እወቁልኝ እያለች ነው፡፡

በቅርቡ በኒውዮርክ በተካሄደው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት በድርጅቱ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በኩል፣ ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ መልማት የሌሎችም እህት ሀገራት መልማት እንደሆነ እንደምታምንና ግብጽን የመጉዳት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላት አረጋግጣለች፡፡ አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ግድቡን የመገንባቷ ልማታዊ እንድምታ እስከ ምን ድረስ እንደሆነም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባች ያለችው ዓለም አቀፍ መርህን በመከተል እንደሆነና፣ በአንጻሩ ግብጽ መርህዉን የጣሰ አካሄድ እየተከተለች አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቷንም አብራርተዋል፡፡

በሂደትም ይህንኑ እውነታ ግብጽ ተረድታ የኢትዮጵያን አቋም ወደ ማክበር እንደምትመጣና መልካም ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን እንደምትከተል እምነታቸው እንደሆነም አክለዋል አምባሳደሩ፡፡

ኢትዮጵያ በዚህኛው ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በተደረጉ የመንግስታቱ ድርጅት ጉባዔዎች በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያለውን ሃቅ ከማሳወቋም በላይ ግብጽ አላስፈላጊ ትንኮሳዋን እንድታቆም ስትጎተጉት ተደምጣለች፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሃቅ በመያዟ ለዓለም ማህበረሰብ እውነታውን ከማሳወቅ እንዳልተቆጠበች የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ግብጽ ስትግል፣ ኢትዮጵያም እውነታውን ይዛ ብሳ ተገኝታለች፡፡