ኮሌጁ ከሀኢቲ ዳቦና እንጀራ አምራችና አከፋፋይ ማህበር ጋር በመተባበር ከክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ለተውጣጡ ወጣቶች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።
ሥልጠናው ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር በገጠር ከተሞች የሚስተዋለውን የዳቦ አቅርቦትና ጥራት ጉድለት ለመቅረፍ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዳቦ አመራረትና ስርጭት ዙርያ ኮሌጁ የአጭር ጊዜ ስልጠና እየሰጠ ነው ያሉት በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሆቴልና ቱሪዝም መምህር አቶ ላቃቸው አያልነህ፥ ፍላጎት ያላቸው ዕድሉን መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ኮሌጁ ለወጣቶች የሚሰጣቸው የሙያ ስልጠናዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ስልጠናው ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም በተገኘ የበጀት ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን አክለዋል።
በዚህ ፕሮግራም በክልሉ ከሚገኙ ሦስት ቆላማ ወረዳዎች ከካፋ ዞን ጎባ፣ ከምዕራብ ኦሞ ዞን መኢኒት ጎልዲያ እና መኢኒት ሻሻ የተውጣጡ ሥራ አጥ ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎችን በመለየት፣ በማሰልጠንና በማስተዋወቅ የዜጎችን ኑሮ በሚያሻሽሉ ጉዳይች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የሚገኘው ሀኢቲ ዳቦና እንጀራ አምራችና አከፋፋይ ማህበር በተባባሪነት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የማህበሩ መስራችና ሰብሳቢ አቶ አብዱልቃድር መኮ፥ በክልሉም ሆነ በዞኑ ለሚገኙ በርካታ ወጣቶች በተለያየ ጊዜ የማህበሩን የሥራ ልምድ በማጋራት እና ስልጠና በመስጠት አጋርነቱን ማሳየቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
ለ5 ተከታታይ ቀናት በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር በሚሰጠው ስልጠና ወጣቶቹ መሠረታዊ የዳቦ አመራረት እንዲሁም ስርጭት ሂደቶችን በአግባቡ እንዲቀስሙ ይደረጋል ብለዋል።
በቀጣይም ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ጥራት ያለውን ዳቦ በማዘጋጀት የአከባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎት እዲያሟሉና በሂደቱም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እዲያረጋግጡ ለማስቻል መልካም እድል እንደሆነም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
ከመማር ማስተማር ተግባር ባለፈ የአካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሚዛን ግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) መጭው ጊዜ ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን የምንሸጋገርበት ብሩህ ዘመን መሆኑን ተናገሩ
በተቀሩት አጭር ቀናት ህብረተሠቡ የመራጭነት ካርዱን በመውሰድ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ የጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳና አካባቢው የፌደራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጥሪ አቀረቡ