በጎፋ ዞን ዑባ ደብረጸሐይ ወረዳ ዛባ ከተማ ሚያዝያ 27/2015 ዓም በደረሰው አስከፊ የጎርፍ አደጋ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በርካታ መኖሪያ የቤቶችና መሰረተ ልማቶች መውደማቸው ይታወሳል።
ከተማዋን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት “ቁስሏን አክመን ውበቷን እንመልስ” በሚል መሪ ቃል የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር ተዘጋጅቷል።
በባዛሩ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጋሻያለው ገላ ስንደመር ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ ይበልጥ የሚጠናከር በመሆኑ፥ የዛባን ከተማ በህብረትና በአንድነት ለማልማት ባለሀብቶች የንግዱ ማህበረሰብ የአከባቢው ነዋሪዎችና የልማት አጋሮች ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ በበኩላቸው፥ የዛባ ከተማ ከደረሰባት አስከፊ አደጋ አገግማ ቀደም ሲል ወደነበረችበት ክብሯ ለመመለስ በጋራ ማልማት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የዞኑ አስተዳደር እና በስሩ ያሉ 12 የከተማና ወረዳ አስተዳደር መዋቅሮች በጋራ በመሆን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ምናሴ ገልጸዋል።
የዑባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እልቶ እፀና አካባቢው በሰሊጥ፣ በዱባ ፍሬ፣ በበቆሎ በቀንድ ከብትና በፍየል ምርት በዞኑ ተጠቃሽ በመሆኑ አልሚ ባለሀብቶች ይህንን ሀብት ወደ ተሻለ ዕድገት ለመቀየር መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ለሶስት ቀናት በተዘጋጀው ባዛር በሚገኘው ገቢ ከተማዋን የመንገድ ዳር መብራት ለማስገባት የውስጥ ለውስጥ መንገድና የጎርፍ መውረጃ ዲች ለመስራት የኮሪደር ልማትና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱን ተናግረዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዱልወዱድ ሰይድ፣ አቶ ሳሙኤል ሳብራ እና መ/ርት ዘላለም በፍቃዱ በሰጡት አስተያዬት ከተማዋን ለማልማትና ለማሳደግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የእስካሁን አፈፃፀም እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለፀ
የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ