ሀዋሳ፡ የካቲት 16/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ማህበሩ የሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል ሆነ ለከተማው ልማት የራሱን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ ገለጹ፡፡
ካራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ሁለገብ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር የምስረታ ጉባኤ በይርጋጨፌ ከተማ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ፥ ህብረት ሥራ ማህበሩ የአባላት ቁጥር ማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ ጥራት ያለውን ምርት ማቅረብ እና የፋይናንስ ግልጸኝነትን ማስፈን ላይ በትኩረት መሥራት አለበት ብለዋል።
ማህበሩ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ዕድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል ሆነ ለከተማው ልማት የራሱን ሚና መወጣት እንዳለበት ያነሱት ከንቲባው፥ በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የጌዴኦ ዞን ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘመናይ ህርባዬ፥ ከዚህ ቀደም ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት በዞኑ ባለመኖራቸው ብዙውን ጊዜ ሲገመገም መቆየቱን አንስተው አሁን ላይ ጠንካራ ህብረት ሥራ ማህበራት እየተደራጁ መሆናቸውንና ማህበሩ ጠንክሮ በመሥራት ለሌሎች ተምሳሌት መሆን አለበት ብለዋል።
የህብረት ሥራ ማህበር መስራች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደግፌ ተፈራ፥ የማህበሩ ዋና ዓላማ ገበያን ማረጋጋትና በአከባቢው የሌሉ ምርቶችን በማቅረብ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን ከአምራቹ ቀጥታ ወደ ማህበረሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል።
ማህበሩ 252 አባላት ይዞ የተደራጀ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፥ በቀጣይ አባላትን በማብዛት እና የራሱን ሱቆች በመክፈት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
የማህበሩ አባል የሆኑት ወይዘሮ አማረች ባህሩ እና አቶ በላቸው ጅግሶ እንደተናገሩት፥ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ያለው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑ፥ ከራሳቸው አልፈው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አባል ለመሆን እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም ማህበሩን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አክለው ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አከራካሪ የሆኑ ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ውሣኔ አስተላለፈ
የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ችግር ፈቺ ሥራዎች ላይ ስልጠና በመስጠት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገለጸ
በጎፋ ዞን የዛባ ከተማ ከደረሰባት አስከፊ አደጋ አገግማ ወደነበረችበት ክብሯ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ