የጠቢቡ ልጆች

በይበልጣል ጫኔ

ድሮ ነው አሉ÷ አንድ ጠቢብ ሰው ተነሳ። ይኼ ጠቢብ ለማንኛውም ሰው÷ ለሹማምንቱም ብልሃት አፍላቂ ሆነ። አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር÷ እሱን አማክሩት የማይል የለም። አንዳንዶቹ እንደውም አድናቆታቸውን ሲገልጡ፦

“የዘመናችንን የጠቢብ ርሃብ ፈጣሪ አይቶ÷ ጠቢቡ ሰሎሞንን ዳግም አስነስቶልን ነው” ይሉታል።

እንዲያ ቢሉትም÷ የሚያንስበት አይነት አይደለም÷ ሰውዬው። ምክንያቱም በሱ ምክር የተፈታ ችግር÷ በዳይንም ተበዳይንም እኩል የማስደሰት ኃይል ነበረው።

በአንድ ወቅት ማዶ ለማዶ የሚተያዩ ሥፍራዎችን የሚያስተዳድሩ ሀገረ ገዢዎች÷ ክፉኛ ተጣሉ። እርግጥ የጠባቸው መነሻ ምክንያት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ነገራቸው ላይ “ነገር ሰሪ” ገብቶበት የአንዱን ከአንዱ እያማታ አቃቃራቸው። ኋላም ውረድ እንውረድ ተባባሉ።

ይኼኛውም ጦሩን ይስላል። ያኛውም ጎራዴውን ይስላል። እዚህ “ብምረው አይማረኝ” እየተባለ ይፎከራል። እዚያም ነገሩ ተጋግሏል። የኋላ ኋላ ሀገረ ገዢዎቹ ከተጣሉበት ጉዳይ ይልቅ÷ ራሳቸው ቃል እስረኛ ሆኑ።

“አሁን ይኼንን ሁሉ ዛቻ እና ፉከራዬን የሰማ ሁሉ÷ ሳልዘምት ብቀር ምን ይለኛል?” አይነት ሃሳብ÷ በግራም በቀኝም የተሰለፉትን ወደ ፍልሚያው ሜዳ ገፋቸው። በዚህም በዚያም ቢለመኑ አሻፈረኝ አሉ። በእርግጥ ቢቀሩ ደስ ሳይላቸው የሚቀር አይመስለኝም። ፎክሮ መቅረት የጀግና ደምብ ስላልሆነ እንጂ።
በዚህ መካከል ጠቢቡ ሰው ነገሩን ሰማ። ሰማና÷ ፈረሱን ጭኖ ገሰገሰ። ገሰገሰና ደረሰ።

ወደ አንደኛው ጦር ሰባቂ ገብቶ ጥቂት አነጋግሮት እንደወጣ÷ ሰውዬው ጦር መስበቁን ተወ። ደግሞ ሄደ÷ ወደሚቀጥለው። እዚያም እንዲሁ አደረገ። ያኛውም “አብራችሁኝ ዝመቱ” ብሎ የሰበሰባቸውን ሁሉ ወደየመጡበት መለሰ።

ይህ ሁሉ እንዴት እንደሆነ ማንም አላወቀም። ነገሩ ቆይቶ ሲሰማ÷ ወደ ሁለቱም ጋ ሄዶ የነገራቸው አንድ እና ተመሳሳይ ሃሳብ ነበር። እዚህም እዚያም፦

“የተናቅኩ ስለመሰለኝ ተናድጄ እንጂ÷ ከጦርነቱ ይልቅ ወንድምነትህ ይበልጥብኛል” ብሎሃል አላቸው ለሁለቱም። በዚህች ቀላል መሳይ ሃሳብ ጠቢቡ ደም መፋሰስ እንዳይኖር አደረገ።

“ዳሩ ምን ይሆናል?” ይላሉ÷ የጠቢቡ የዘመን ተጋሪዎች፦

“ዳሩ ምን ይሆናል?÷ ‘የእሳት ልጅ አመድ’ እንዲሉ÷ ጠቢቡ ልጅ አልወጣለትም” እያሉ ያሙታል። በሚገርም ሁኔታ÷ ለሌላው የሚተርፍ ቀርቶ ለራሳቸው የሚኖሩበት ጥበብ የሌላቸው ነበሩ÷ ልጆቹ። የዚያ ዘመን ነዋሪዎች “እውን አንተን ወለደ?” የሚለውን ÷ይኼንን የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራን ግጥም አግኝተውት ቢሆን÷ እንድሚጋብዟቸው ጥርጣሬ የለኝም፦
…..
ያ አባትህ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
ማን ይሙት አንተን ወለደ?
“አባቴ ይሙት” እንዳትለኝ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ
ትጉህ ወራሽ በማጣቱ
ቦዩ በመገደቡ ጉዞው በመገታቱ
የሱ እረፍት ሞት አይደለም÷ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ …..
አንድ ወቅት የልጆቹ ስንፍና ያበሳጨው ጠቢቡ ሰው÷ ቁጭ አድርጎ ይመክራቸው ጀመር፦
“እንዴት መኖር እንዳለባችሁ ከተፈጥሮ ተማሩ። ጉንዳኖች በጣም ጥቃቅን ነፍሳት ናቸው። ግን ደግሞ ብልህ ናቸው። በበጋ ወቅት ለክረምት የሚሆናቸውን ምግብ ይሰበስባሉ። ሰው እንዴት እነሱን አይቶ እንኳን÷ ስለ ነገ ህይወቱ አይጨነቅም?

አይጦች ወዲህ ወዲያ ብለው የዕለት ጉርሳቸውን ይፈልጋሉ። ቀበሮ አይጦችን ካየ አሳዶ ይይዛቸዋል። ቀበሮ በራሱ ግን ከነብር አሊያም አንበሳ እራትነት አይዘልም። ሰው ይኼንን አይቶ እንዴት አይማርም?

ጠንክራችሁ ራሳችሁን ማኖር አለባችሁ። ጠላት ቢገጥማችሁ ተባብሮ መመከት ይገባችኋል። ጠላታችሁን ድል እንደማታደርጉት ከገባችሁ÷ ወዳጃችሁ አድርጉት። ለወዳጅነት ካልተመቸ ግን ሽሹት። መኖሪያችሁ ከትልልቆች ጋር ይሁን። ከትልቅ ጋር መዋል ያልቃል። ከትንሽ ጋር መዋልም ያሳንሳል”

እያለ ብዙ መከራቸው። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሲያያቸው ግን ልጆቹ በምስር ወጥ እየተጣሉ ነበር። “እንጀራዬን ወሰደብኝ፣ ምስር ወጤን ጨረሰብኝ …” እየተባባሉ። አባታቸው እንደዚህ ቀን ተስፋ ቆርጦባቸው አያውቅም።

ዛሬ ላይ ጠቢቡም÷ የጠቢቡ ልጆችም የሉም። ኧረ የልጅ ልጆቹም የት እንዳሉ የሚያውቅ የለም። ምናልባት ከተርታው ሰው ጋር ተቀላቅለው÷ ተራ ኑሮ እየገፉ ይሆናል። በእርግጥም “ከትልቅ መወለድ ሙያ አይደለም÷ ራስን ለትልቅ ቁም ነገር ማብቃት እንጂ” አይደል የሚባል?

ባይሆን÷ ስለ ምስር ወጥ ካነሳን አይቀር÷ አንድ ጨዋታ ልንገራችሁማ፦
ሁለት ሰዎች ተጣልተው ነው÷ አሉ። ሃብታም እና ድሃ ናቸው÷ ሰዎቹ። ድሃው ሰውዬ ብስጭት ብሎ ተናገረ፦
“ምንም ያህል ሃብት ቢኖርህ ልትመካበት አይገባም። እኔም አንተም በማዕድ ስንቀመጥ ከአንድ እንጀራ በላይ አንበላም” አለ።

ሃብታሙ ሰውዬ ፌዘኛ ቢጤ ነው። በድሃው ሰው ንግግር እየሳቀ፦

“እንጀራው ሁሉ እንጀራ ከሆነ ልክ ነህ÷ ከአንድ እንጀራ በላይ ላንበላ እንችላለን። ከቻልክ ግን እንጀራውን ትተን ስለ ወጡ እናውራ” ብሎ መለሰለት።

ወዳጄ÷ ይኼን ነገር እንዴት ታዋለህ?÷ የኛ ተረት “ሆድ ባዶ ይጠላል” ቢሆንም÷ የወጥ ነገር የኑሮ ማሳያ እየሆነ ነው። አንተ ተሟሙተህ የድሃ ተዝካር የመሰለ ሠርግ ትደግሳለህ። ጎረቤቶችህ ደግሞ÷ ተዝካራቸው ስም ያለውን ሠርግ የሚያስንቅ ሆኗል።

መቼም በቅርቡ እየሆነ ያለውን ሳትታዘብ የቀረህ አይመስለኝም። በታዋቂ ሆቴል ምግብ አቅራቢነት÷ በሰለጠኑ ባለሙያዎች አስተናጋጅነት ነው “የፍራጅ እህል” እየቀረበ ያለው።
አንድ ቤት ከቀብር መልስ እንዲህ ባለ የተትረፈረፈ ድግስ÷ ቀባሪው በምግብ ሲራጭ የተመለከተ አልፎ ሂያጅ “ሟች በጣም አናዷቸው ነበር እንዴ” ማለቱን የሰማሁ ቀን ሆዴን ይዤ ነው የሳቅኩት።

አንድ ወዳጃችን÷ የሆነ ጊዜ ቤት መግዛት ፈልጎ አማከረኝ። እኔም ሲሉ በሰማሁት መልኩ መከርኩት፦

“ቤት የሚገዛ ሰው÷ ቤት ብቻ ሳይሆን ጎረቤትም ጭምር ነው አብሮ የሚገዛው። እንደ አቅምህ የምትኖርበት÷ ጥሩ ማህበራዊ ህይወት ያለበት ቦታ መርጠህ ግዛ” አልኩት። እሱም መልሶ፦

“ዋጋ ከፍዬም ቢሆን÷ ውድ ሰፈር ነው መኖር የምፈልገው። መኪና ባይኖረኝም መኪና ያላቸው ሰዎች ያሉበት። ጥሩ ጥሩ ፊት የሚታይበት። ምክንያቱም ድሃ ሰፈር ከኖርክ ድህነታቸውን ያወርሱሃል” አለኝ።

እንዳለውም አቅሙን አሟጦ÷ የሀብታሞች ጎረቤት ሆነ። ጎረቤቶቹ ባለትላልቅ ግንብ እና ባለ አደገኛ አጥር ናቸው። መንደራቸው ንፁህ እና ውብ ቢሆንም÷ ሰው አይታይበትም። ከወራት ቆይታ በኋላ
“ለመድክ ወይ?” አልኩት።

“ሰፈሩንስ ለምጄዋለሁ። የወጣቸው ሽታ ግን ሊያኖረኝ አልቻለም” አለኝ።

እና ምን ልላችሁ ፈልጌ ነው?÷ ያለ አቅማችሁ ትከሻ አትለካኩ። አትፎካከሩ።