የእንሰት ሰብል ዝሪያን በማሻሻልና ምርትን በዘመናዊ መንገድ በማበልጸግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

ችግር ፈቺ የእንሰት ምርምር ውጤቶች ከህብረተሰቡ ተጠቃሚነት አኳያ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መሆኑን ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።

በተፈጠረላቸው ምቹ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን በጋሞ ዞን ዶርዜ እና ጨንቻ ከተማ በማህበር የተደራጁ ሴቶች ተናግረዋል።

በዶርዜ ሞዴል የእንሰት ማባዣ ጣቢያ፣ ባህላዊና ዘመናዊ የእንሰት ማምረቻ ቴክኖሎጂዎች፣ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያበለፀጋቸው አዳዲስ የእንሰት ውጤቶችና የምርምር ማዕከላት የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም የእንሰት ሰብል ዝሪያን በማሻሻልና ምርቶችን በዘመናዊ መንገድ በማበልጸግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ ያነጋገርናቸው ከኬንያ የመጡትና በጀሞ ኬንያታ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በባዮ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ግሬስ ዋቸከ፤ የሀገር በቀል ዕውቀትን ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ለማዋል በማለም አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእንሰት ሰብል ላይ የጀመረውን ሥራ በይበልጥ ለማስፋፋት በቅንጅት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የሆርቲ ካልቸር መምህርና የእንሰት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሳቦራ ሻራ እንደተናገሩት፤ በእንሰት ሰብል ላይ የሚከሰተውን አጠውልግ በሽታ በዘላቂነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የእንሰት ምርቶች የጥራት ደረጃቸው በዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎች የተረጋገጡ በመሆናቸው ለውጭ ምንዛሪ የሚውሉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ፍቃዱ ናቸው።

በአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንሰት ዝሪያ ማሻሸያ ተመራማሪና ብሔራዊ የእንሰት ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ሄኖክ ፍቅሬ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ያለውን እንሰት በስፋትና በጥራት በማምረት የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በተፈጠረላቸው ምቹ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን በዞኑ ዶርዜ እና ጨንቻ ከተማ በማህበር የተደራጁ ሴቶች ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሰለሞን አላሶ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን