የእግር ኳስ ክለቦቻችን አስጊ አካሄድ

በኢያሱ ታዴዎስ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ችግር እየተንከባለለ አሁን አስጊ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በስፖርቱ ግዙፍ በሆነው የፕሪሚየር ሊግ መድረክ ላይ ሲሳተፍ የቆየው ወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ችግሩ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማሳያ ሆኗል፡፡

በቅርቡ ወልቂጤ ከተማ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስነ ምግባር ደንብ መሰረት ተገቢውን መስፈርት ባለማሟላቱ ከሊጉ መሰረዙ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጥ አንድ ክለብ ለ2017 የውድድር ዘመን የክለብ ላይሰንሲንግ ምዝገባውን ካከናወነ በኋላ የተቀመጡ መስፈርቶችን ስለማሟላቱ ምርመራ እንደሚደረግና መስፈርቶች ካልተሟሉ ቀነ ገደብ ተሰጥቶት እንዲያሟላ፣ ካልሆነ ግን የተላለፈውን ውሳኔ እስኪፈጽም ድረስ ከዝውውር እንቅስቃሴ እገዳ፣ ማስጠንቀቂያ እና የገንዘብ ቅጣት የሚያስከትሉ የቅጣት ዝርዝሮች መቀመጣቸውን ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም መስፈርቶቹን ሳያሟላ ቀነ ገደቡ ካለፈ ሌሎች ቅጣቶች ተከትለው እንደሚመጡ ያትታል፡፡

ከወልቂጤ ከተማ ጋር በተያያዘም ክለቡ እስከ ቀነ ገደቡ ማብቂያ መስከረም ወር ድረስ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ዜጋ ተጫዋቾች ያልተከፈለ ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ማጠናቀቁን የሚያሳይ ሰነድ ባለማቅረቡ የተጫዋቾች ዝውውር ሳያካሂድ የውድድር ዓመቱን መጀመሩን የፌደሬሽኑ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡

ቀነ ገደቡ ካለፈበት መስከረም 8 በኋላም በቅጣት መስፈርቱን ማሟላት ባለመቻሉ ከክለብ ላይሰንሲንግ በተጨማሪ በፊፋ የተጣለበት የዝውውር እገዳ ባለመነሳቱ ለሁለተኛው የሊጉ የጨዋታ መርሃ ግብር ተጫዋቾችን ማስመዝገብ ስላለመቻሉም ተገልጿል፡፡

ይህም በመሆኑ የሊጉን ሁለት መርሃ ግብር ጨዋታዎችን ባለማድረጉ የፎርፌ ሕግ ተግባራዊ መደረጉን የፌደሬሽኑ መግለጫ ያሳያል፡፡

ከዚህም መነሻ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስነ ምግባር መመሪያ ክፍል 3 አንቀጽ 69 ንኡስ አንቀጽ 3 ተራ ቁጥር 14 መሰረት ከሚወዳደርበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሰረዙን ይፋ አድርጓል ፌደሬሽኑ፡፡

መቼም የወልቂጤ ከተማ ጉዳይ ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን አይመለከትም ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በሊጉ የተጫዋቾችን ደመወዝ በየወሩ ለመክፈል እየተቸገሩ ያሉ ክለቦች ስለሚገኙ፡፡

ለክለቦች ወልቂጤ ከተማ የገጠመው ጉዳይ እንደ ማንቂያ ደወል ነው፡፡ ነገ ማን ይከተል አይከተል በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡

ክለቦችን ለዚህ ሁሉ ችግር ያበቃቸው የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ በቂ ገቢ ያለመኖር፡፡ አሁን የሀገራችን ክለቦች ያሉበት የገቢ ደረጃ በአውሮፓዊያኑ ልክ የሚመረመር ቢሆን ኖሮ የትኛውም ክለብ ከውድድሮች ከመታገድ አይተርፍም ነበር፡፡ ወጪን ከገቢ ጋር የማመጣጠን ሕገ ደንብ (ፋይናንሺያል ፌይር ፕሌይ) ጥቅም ላይ እየዋለ በመሆኑ፡፡

በእርግጥ እግር ኳሷ ከመዝናኛ አልፎ ረብጣ ቢሊየን ዩውሮዎች የሚዘዋወሩበት ኢንደስትሪ ወደ መሆን ያደገው አውሮፓን፣ ገና ዳዴ ማለት እንኳን ካልጀመረው ኢትዮጵያ ጋር ማነጻጸሩ በራሱ እንደ ወንጀለኛ ሊያስቆጥር ይችላል፡፡

ነገር ግን የአውሮፓ ክለቦች ራሳቸውን ጤናማ በሆነ የገንዘብ ፍሰትና አቅም በማደራጀት ውጤታማ ለመሆን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ከእነሱ መኮረጁ ወንጀለኛ አያስብልም፡፡

ከዚህ አመክንዮ መነሻ አብዛኞቹ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ጤናማ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው በምን ዓይነት መልኩ የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግ ይጥራሉ የሚለውን መመልከቱ አይከፋም፡፡

እርግጥ ነው ክለቦች ገቢያቸውን ለማሳደግ በምንጭነት የሚጠቀሟቸው ዘርፎች እንደየሊጎቹ እና እንደየሀገራቱ ደረጃ እንደሚለያይ እሙን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአውሮፓ የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች ሁሉ ተመሳሳይ ስልት ይጠቀማሉ ማለት እንዳልሆነ ከግንዛቤ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡

ቢሆንም ግን በጥቅሉ ተመሳሳይ ስልት ስለሚጠቀሙና ይኸው ስልት በዘመናዊው እግር ኳስ እንደ ግዴታ እየተቆጠረ ስለሚገኝ ስልቶቹን የጋራ አድርጎ ለመጥቀስ እንገደዳለን፡፡

የእግር ኳስ ክለቦች ራሳቸውን በገቢ ለማደርጀት በዋነኛነት አራት ዓይነት የገቢ ምንጮችን ይጠቀማሉ፡፡ የቀጥታ የስርጭት መብት፣ የጨዋታ ቀን እና የቲኬት ሽያጭ ገቢ፣ የንግድና ግብይት እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ፡፡

የቀጥታ የስርጭት መብት በዋነኛነት የቴሌቪዥን ሽያጭ መብትን የተመለከተ ሲሆን የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች እና ሊጎችን ካዝና የማደለብ አቅም አለው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ የሊግ ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ አስተላላፊ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ተወዳድረው ካሸነፉ በኋላ የውድድሮቹ ይፋዊ መብት ባለቤቶች ይሆናሉ፡፡

ክለቦችም ከሚያደርጓቸው የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተሳትፎ መነሻ፣ ጨዋታዎቻቸው ታሳቢ ተደርጎ ከስርጭቱ ከሚገኘው ገቢ የድርሻቸውን ያገኛሉ ማለት ነው፡፡

የእግር ኳስ ክለቦችን ከስፖርቱ በሚያገኙት ገቢ ደረጃቸውን በመመደብ የሚታወቀው “ድሎይት ፉትቦል መኒ ሊግ” በአውሮፓዊያኑ 2021 ባወጣው ሪፖርት መሰረት እንደ እንግሊዝ ያሉ ታላላቅ ሊጎች ከቴሌቪዥን ስርጭት መብት የሚያገኙት ገቢ ሰማይ እየነካ መጥቷል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ የዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ስርጭት ገቢ በ1992 40 ሚሊየን ፓውንድ የነበረው፣ በ2021 ወደ 3 ነጥብ 83 ቢሊየን ፓውንድ ማደግ ችሏል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉም የቴሌቪዥን ስርጭት መብት ጨረታውን በየሶስት ዓመቱ ያደርግና በ6 የተለያዩ ጥቅሎች ይሸጣቸዋል፡፡

ታዲያ በዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው የስርጭት ገቢ 50 በመቶ የሚሆነው በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ለሆኑ 20ውም ክለቦች እኩል ድርሻቸው ይሰጣቸዋል፡፡ 25 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በውድድር ዘመኑ ክለቦች በሚቀመጡበት የደረጃ ሰንጠረዥ ልክ በሽልማትነት ይበረከታል። ቀሪው 25 በመቶ ክለቦች ያካሄዱት እያንዳንዱ ጨዋታ ተሰልቶ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

በዚሁ ስሌት ነው ዛሬ ላይ የእንግሊዝ ክለቦች ካዝናቸው ደልቦ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ገበያ እንደተከፈተ ያለስስት እንዲሳተፉ የሚያደርጋቸው፡፡ ይህ በሌሎችም ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለ አሰራር ነው፡፡

ሌላኛው የጨዋታ ቀን እና የቲኬት ሽያጭ ገቢ ነው፡፡ ይህ ጨዋታ በሚካሄድበት ቀን ከስቴዲየም አገልግሎቶች (በስቴዲየሙ ዙሪያ የሚሸጡ ምግብ እና መጠጦች… ሌሎችም) እንዲሁም ከቲኬት ሽያጭ የሚገኙትን ገቢዎች ያጠቃልላል፡፡

በ1992 የጨዋታ ቀን አማካይ ገቢ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አጠቃላይ ገቢን 43 በመቶ የሸፈነ ነበር፡፡ በ2021 የጨዋታ ቀን ገቢ በሶስት እጥፍ ቢያድግም የሊጉን አጠቃላይ ገቢ 13 በመቶ ነው የሸፈነው፡፡

ይሁን እንጂ ክለቦች በአውሮፓ እና በሀገር ውስጥ ውድድሮች በሚያደርጓቸው ተሳትፎዎች እና እንደ ሚሰጡት አገልግሎት አቅም የጨዋታ ቀን ገቢያቸው ይለያያል፡፡

… ይቀጥላል